በቤንች ማጂ ዞን ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለፀ

89
ሚዛን ነሀሴ 6/2010 በቤንች ማጂ ዞን ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው ግጭት መፍታት እንደሚገባ በዞኑ የተለያየ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ የቤንች ማጂ ዞን የሠላምና ጸጥታ ምክር ቤት ጉባኤ  የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ትናንት በሚዛን ከተማ ተካሄዷል፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል ከሱርማ ወረዳ የመጡት አቶ ባርኮይ ወለቻንጊ እንዳሉት በሱርማ ወረዳና አካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ለዓመታት የቆየና አሁንም ያልተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በሱርማ የአርብቶ አደር አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ የመሠረተ ልማት ችግር መኖሩን የገለፁት አቶ ባርኮይ ይህም ለጸጥታ ችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መንግስት ለሠላም መደፍረስ ምክንያት ለሚሆኑ ገዳዮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የህብረተሰቡን በሰላም የመኖር መብት ማረጋገጥ እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡ በብሔረሰቡ ስም ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በመለየትም ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ ከደቡብ ቤንች ወረዳ የመጡት አቶ ስንታየሁ ጋይድ በበኩላቸው በወረዳው በበርካታ ቀበሌዎች የመንግስት መዋቅር አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት የመንገድ፣ መብራትና የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እንደሚሰራላቸው ቃል ቢገባላቸውም ተግባራዊ አለመደረጉ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡ መንግስት የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎትና ጥያቄ በአግባቡ ካለመመለሱ ጋር ተያይዞ በአካባቢው የመልካም አስተዳደር ችግር በመሆን ለግጭት መንስኤ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ የቤንች ማጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት አሰፋ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጉዳዮች በሰጡት ምላሽ አግባብነት ያላቸው የሕዝብ ጥያቄዎች ተለይተው  ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡ በህብረተሰቡ የሚነሳ ማናቸውም ጥያቄና ቅሬታ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሊያቀርብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በዞኑ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡ በመድረኩ ላይ ከድንበር፣ ከህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ከዞን አስተዳደር ጋር ተያያዞ በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም