በታዋቂ አትሌቶች የሚዘጋጀው ዓመታዊ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነሐሴ 13 በመቀሌ ከተማ ይካሄዳል

67
አዲስ አበባ ነሃሴ 6/2010 በአትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያምና አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ የሚዘጋጀው ዓመታዊው አገር አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ ይካሄዳል። የጎዳና ላይ ሩጫው ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮው ውድድር 'ወጋገን ናትና የጎዳና ሩጫ' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በውድድሩ ላይ 15 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ውድድሩ መነሻውንና መድረሻውን በሮማናት አዳባባይ አድርጎ በመቀሌ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የሚካሄድ ይሆናል። ሁለቱ ታዋቂ አትሌቶች በ2009 ዓ.ም 'ናትና ስፖርት ኤቨንትስ' ድርጅት ያቋቋሙ ሲሆን የተለያዩ ሩጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ኩነቶችና ፌስቲቫሎችን ማካሄድ ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ ነው። የናትና ስፖርት ኤቨንትስ ድርጅት መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም ለኢዜአ እንደገለጸው የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ በክልሉ ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር እድልና አማራጭ ለመፍጠር ነው። በክልሎች በሚገኙ ክለቦችና ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚገኙ አትሌቶች በየዓመቱ የሚያገኙት የውድድር ቁጥር በቂ እንዳልሆነና በዚህ ረገድም የጎዳና ሩጫው መካሄድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት ተናግሯል። በዘንድሮው ውድድር የህጻናት ሩጫ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድና ከ7 እስከ 14 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት በ800 ሜትርና በሁለት ኪሎ ሜትር ተከፋፍለው እንደሚሮጡ ነው አትሌት ገብረእግዚአብሔር የገለጸው። በጎዳና ላይ ሩጫው በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ አትሌቶች በቅደም ተከትል የ50፣ የ30ና 20 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚሰጥም ጠቁሟል። የ10 ኪሎ ሜትሩን የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ናትና ስፖርት ኤቨንትስ ድርጅት፣ የመቀሌ ከተማ አስተዳደር፣ የትግራይ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ወጋገን ባንክና ሌሎች አጋር አካላትም በጋራ የሚያዘጋጁት ይሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም