በማንነትና በሀይማኖት ተቋማት የተፈፀመውን ጥቃት እናወግዛለን፤-የነገሌ ከተማ ነዋሪዎችና የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች

74
ነገሌ ነሀሴ 6/2010 ለፖለቲካ ትርፍ በማንነትና በሀይማኖት ተቋማት ላይ የሚፈጸም የሀይል ጥቃት እንደሚያወግዙት የነገሌ ከተማ ነዋሪዎችና የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ገለጹ፡፡ በጂጂጋ ከተማ ሰሞኑን የተፈጸመው እኩይ ተግባር ማንኛውንም ሀይማኖት የማይወክልና ከሀይማኖት አስተምሮት ውጭ በመሆኑ አጥብቀው እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል፡፡ የነገሌ ከተማ ነዋሪ የጉጂ ዞን ሸሪአ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የእስልምና ሀይማኖት አባት ሼህ ከድር አብዱረህማን “የእስልምና ሀይማኖት እንደ ስሙ ሰላም ማለት ነው'' ብለዋል፡፡ የሀይማኖቱን ህግጋት አስተምሮትና የቅዱስ ቁርአን ቃል የማያከብር የፈጣሪው ባለእዳ እንደሆነና በመጨረሻውም አስከፊ የነፍስ ሞት እንደሚጠብቀው አብራርተዋል፡፡ በጽንፈኝነት አስተሳሰብ በማንነትና በሀይማኖት ተቋማት ላይ በደል በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ መንግስት አስተማሪ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ “የሀይማኖት መሪዎች ተከታዮቻችን በበቀል ርምጃና በሌላም ዳግም መሰል ጥፋት እንዳይፈጸም የማስረዳትና የማስተማር ድርሻ እንወስዳለን'' ብለዋል፡፡ ሌላው የነገሌ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ አብዲ አሊም መንግስት ህግና ህገመንግስታዊ ስርአቱን የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ በማን አለብኝነት በጠራራ ጸሀይ የሰው ህይወት የሚያጠፉ፣ ንብረት የሚያቃጥሉና የሚዘርፉ ጥቂት ጸረ ሰላም ቡድኖችና ግለሰቦች በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ “ሀገራዊና ሰላማዊ ለውጡን የተቀበልን የሀገር ሽማግሌዎችና ወላጆች ወጣቶችና ልጆቻችንን አስተምሮና መክሮ መመለስ ይጠበቅብናል'' ብለዋል፡፡ “በሀይማኖት ሽፋን የሚፈጸም የሀይል ጥቃት በመንግስት ብቻ የሚቆም ባለመሆኑ የድርጊቱን ተዋናዬች በመታገል፣ በማጋለጥና ለህግ አሳልፎ በመስጠት የድርሻችንን እንወጣለን'' ብለዋል፡፡ የሰላምና የሀገር ግንባታ ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁላችንም ድርሻ ሊኖረን ይገባል ያሉት ደግሞ የነገሌ ከተማ ነዋሪ አቶ ዲዳ ገልገሎ ናቸው፡፡ በመሆኑም በየአካባቢው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን መንግስትና ህዝብ ተመካክረው ሊሰሩ እንደሚገባም መክረዋል፡፡ አሁን የተገኘውን ሰላም ለመጠበቅ ህብረተሰቡ ራሱን ከጥፋት በማራቅ የድርሻውን እንዲወጣ በየጊዜው የእርስ በርስ ምክክርና ውይይት ማደረግ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡ ከቀበሌ እስከ ዞን ያሉ አመራሮችም ከህዝብ የሚቀርብላቸውን አስተያየት፣ ጥያቄና ጥቆማ በመቀበል ፈጣን የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ በጂጂጋ የደረሰው በማነነትና በሀይማኖት ተቋማት ላይ  ያነጣጠረ ጉዳት ዳግም እንዳይፈጠር መንግስት በጥፋተኞቹ ላይ አስተማሪ የቅጣት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም