ተምችን በመቆጣጠር የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት እንደሚገባ ተጠቆመ

700

ደብረ ብርሃን ነሃሴ 6/2010 በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውን ተምች በመቆጣጠር የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ማሳከት እንደሚገባ የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በዘርፉ የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በደብረ ብርሃን ከተማ መክሯል።

የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢያሱ አብረሃ በዚህ ወቅት እንዳሉት የግብርና ምርታማነትን በማሳድግ ለኢንዱስትሪው የሚሆን ግብዓት ለማቅረብ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።

በዚህም በመኽር እርሻው 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለኢንዱስትሪና ለምግብነት በሚውሉ የበቆሎና የማሽላ ሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ ዞኖች በበቆሎና በማሽላ ከተሸፈነው ሰብል ውስጥ 490 ሺህ 385 ሄክታሩ በተምች መጠቃቱንና ተምቹን ለማስወገድ እስካሁን በተደረገው ርብርብ ከ106 ሺህ በሚበልጥ ሄታር ላይ የተከሰተውን ተምች መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ኢያሱ እንዳሉት ተምቹን በማስወገድ ሥራ ላይ 130 ሺህ 218 አርሶ አደሮች በባህላዊ ለቀማ የተሳተፉ ሲሆን 96 ሺህ 156 ሊትር ኬሚካልም ለርጭት ጥቅም ላይ ውሏል።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውን ተምች ለመቆጣጠር የግብርና ባለሙያው ከአርሶ አደሩ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በባህላዊ ለቀማ ዘዴ የማስወገድ ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካም ሰብሎችን በመከታተልና በመቆጣጠር ተምችን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ሁሉም በትኩረት አንዲሰራ ሚንስትሩ አሳሰበዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ በበኩላቸው በክልሉ በበቆሎና በማሽላ ሰብሎች ከተሸፈነው ከ550 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ በ62 ሺህ 808 ሄክታር ማሳ ላይ ተምች ተከስቷል።

“በተምቹ የከፋ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች 15 ሺህ 404 ሊትር ኬሚካል በመርጨትና 30 ሺህ አርሶ አደሮች በባህላዊ መንገድ በለቀማ ለማስወገድ በተደረገው ጥረት 52 ሺህ 145 ሄክታሩን መቆጣጠር ተችሏል” ብለዋል፡፡

የመከላከል ዘዴውን ለማጠናከርም በየ15 ቀኑ ከዞን ግብርና በለሙያዎች ጋር መረጃ የመለዋወጥና አዳዲስ አቅጣጫዎችን የማስተላለፍ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ግብርናና እንስሳት ሀብት ቢሮ የኢንስፔክሽን አገልግሎት አሰጣጥና የግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀሐይ አዳሙ በበኩላቸው በክልሉ በዘር ከተሸፈነው 125 ሺህ የበቆሎና የማሽላ ሰብል ከ12 ሺህ ሄክታር በሚበልጠው ላይ ተምች ተከስቷል፡፡

አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በባህላዊ መንገድና በኬሚካል ለመከላከል በተደረገ ጥረት ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት ከተምች ነጻ ለማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተያዘው የመኸር እርሻ ታርሶ በዘር ከተሸፈነው 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 375 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡