በሀረሪ ክልል ከ63 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባ ፕሮጀክት ተመረቀ

96

ሐረር፣ ነሐሴ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሀረሪ ክልል ከ63 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የሀረር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በምረቃው ወቅት እንደተናገሩት፤ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ሁሉም በባለቤትነት ሊንከባከበው ይገባል።

የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ክልሉ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱ ወጣቶችን በሙያና በክህሎት ለማዳበር አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

“በክልሉ ያሉ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ስልጠና አግኝተው ወደ ስራ እንዲገቡ ኮሌጁ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል” ብለዋል።

“በኮሌጁ የሚሰጡ ስልጠናዎች የገበያ ፍላጎትን ያገናዘቡ ሊሆኑ ይገባል” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ሰልጣኞች ተገቢውን ክህሎት እንዲጨብጡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በርካታ ወጣቶችን በማሰልጠን ወደ ስራ እያሰማራ ያለው የሀረር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሚልኬሳ አህመድ “የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የኮሌጁን የቅበላ አቅም ያጎለብታል” ብለዋል።

ተገንብቶ በተጠናቀቀው ህንፃ ከጀርመን በተገኘ የ46 ሚሊየን ብር ድጋፍ የአውቶሞቲቭ እና የኤሌክትሪካል የስልጠና ትምህርት ክፍሎች በመሳሪያዎች መሟላታቸውን ጠቁመዋል።

በእለቱ በሀረር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም