የምግብ ዘይትና ስኳር በህገወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

59
ደብረ ብርሃን ነሀሴ 6/2010  የምግብ ዘይትና ስኳር በህገወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የተገኙ አምስት ግለሰቦች እስከ ዘጠኝ ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ። የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሪት ዘርትሁን ያዘው ለኢዜአ እንደገለጸችው የምግብ ዘይትና ስኳር በመንግስት ድጎማ ለህብረተሰቡ የሚቀርብ ነው። ይህ እየታወቀ ያለንግድ ፈቃድ የምግብ ዘይትና ስኳር በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ በተገኙ አምስት ግለሰቦች ላይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጥፋተኛነታቸውን በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጦ ከሰባት እስከ ዘጠኝ ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ በይኖባቸዋል። አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሾች አቶ ጥላየ ተጋፋው እና አቶ አለም እሸት ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም 60 ኩንታል ስኳር በአይሱዙ የጭነት መኪና ሲያዘዋውሩ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተረጋግጧል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት በግለሰቦቹ ላይ የዘጠኝ ዓመት እስራት እንዲሁም ከ155 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ስኳር ሽያጭና በዋስትና ያስያዙት ብር ለመንግስት ገቢ እንዲሆንም ተበይኖባቸዋል። በተጨማሪም መስከረም 9 ቀን 2010 ዓ.ም በሚዳ ወረሞ ወረዳ 300 ጀሪካን የፓልም የምግብ ዘይት በመኪና ሲያዘዋውሩ በቁጥጥር ስር በዋሉ ሦስት ግለሰቦች ላይ ፍርድ ቤቱ እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ እስራትና ከ100 ሺህ ብር በላይ ብይን ማስተላለፉን ወይዘሪት ዘርትሁን አስረድተዋል። በግለሰቦቹ ላይ ብይኑ የተላለፈው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ፣ የንግድ ምዝገባ አዋጅና የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅን ጥሰው በመገኘታቸው መሆኑን ከፍርድ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም