የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ህወሓት ግፍና ጫና በመቃወም ለኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ አጋር መሆን አለበት

68

ነሀሴ 20/2013 (ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ህወሓት ግፍና ጫና በመቃወም ለኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ አጋር መሆን እንዳለበት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴል ጄነራል አስረስ አያሌው ተናገሩ።

ብርጋዴል ጄነራሉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ቢሆንም በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና እና በደልም የከፋ ነው።

መንግሥት የትግራይ ህዝብ ወደ ልማት ሥራዎች እንዲገባ በሚል የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም አሸባሪው የህወሓት ቡድን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጦርነት ከፍቷል ብለዋል።

ይህ አሸባሪ ቡድን በተለይም በአጎራባች ባሉ የአማራና አፋር ክልሎች ላይ ትንኮሳና ወረራ መፈጸሙን ነው የተናገሩት።

አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው በእነዚህ አካባቢዎች የመንግሥትና የህዝብ ንብረቶችን በመዝረፍና በማውደም የባንዳነት ተግባር እየፈፀመ መሆኑንም ነው የገለፁት።

ከዝርፊያና ግድያ እና ሴቶችን በመድፈር ከፍተኛ ወንጀል እየፈመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ህወሓት በእምነት ተቋማትና በተከለከሉ ቦታዎች ላይም የጥይት ማጠራቀሚያና ከባድ መሳሪያ ማጥመጃ ከማድረጉም በላይ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ፣  የዘር ማጥፋትና የጦር ወንጀል የፈጸመ ነው ብለዋል።

"አሸባሪው ህወሓት የውጭ ኃይሎች ጥቅም አስከባሪ የዘራፊና ከሃዲ ስብስብ ነው" ያሉት ብርጋዴል ጄነራል አስረስ  ቡድኑ ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው ብለዋል።

በመሆኑም የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ህወሓት የግፍ ጫና በመቃወም ለኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ አጋር መሆን አለበት ብለዋል።

አገር የማዳንና የህልውና ዘመቻ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ሠራዊቱ የተሰጠውን ግዳጅ እንዲወጣ ህብረተሰቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሰው ኃይል፣ በገንዘብ፣ በስንቅ፣ በደም ልገሳ እና በሞራል ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ከቀበሌ እስከ ወረዳ፣ በዞን፣ በክልል እና በከተሞች ኮሚቴዎች ተደራጅተው ለሠራዊቱ ድጋፍ እያሰባሰቡ መሆኑን ገልፀው፤ ህብረተሰቡ ከአገር ህልውና በላይ ምንም የለም በሚል ከፍተኛ እገዛና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው ያስታወሱት።

ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ፤ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም