የሃገሪቱን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ ምሁራን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመለከተ

82
ባህርዳር ነሀሴ 5/2010 የሃገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ  ዳር እንዲደረስ ምሁራን በተደራጀ አግባብ ሃሳብ በማፍለቅና ተግባራዊ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ተወያይተዋል። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የህዝቡን ጥያቄ በዘላቂነት ሊመልስ የሚያስችል የለውጥ ሂደት ውስጥ ተገብቷል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል። ቀደም ሲል መንግስት ከምሁራን ጋር ተገቢውን ግንኙነት ፈጥሮ ሰርቷል ብለው እንደማያምኑና ከምሁራን የሚነሱ ሃሳቦችን ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ ረገድም  ክፍተት እንደነበር ተናግረዋል። " በተበታተነ መንገድ ይደረግ የነበረውን የለውጥ ትግል በማዳከም እንዲሁም እርስ በእርስ ስንበላላ የህዝቡን የትግል አቅም ስናዳክም ቆይተናል፤ በዚህም ህዝቡም ሆነ ሃገር አልተጠቀመም " ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ። በህዝቡ ጠንካራ ግፊት አሁን ላይ ለለውጥ  ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው በዚህ  ማዕበል ውስጥ የምሁራን ድርሻ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ምሁራን በሚፈለጉት መንገድ ተደራጅተው ቢመጡ የክልሉን መንግስት የሚመራው ብአዴን በሚያግባቡ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ በሚያለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ደግሞ ተከባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። በውጭ የሚኖሩ በርካታ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ቢኖሩም አሰባስቦ አቅማቸውን መጠቀም አለመቻሉን አስታውሰው፤ ያለፈውን ጠባሳ መሻር የሚቻለውም በቀጣይ ህዝቡን የሚጠቅም በጎ ስራዎችን በጋራ በማከናወን እንደሆነም ተናግረዋል። "ሁለንተናዊ ለውጥ በምኞት አይመጣም" ያሉት አቶ ገዱ ለውጡ ግቡን እንዲመታ ምሁራን በተሰማሩበት የሙያ መስክ ብቻ ሳይሆን ህዝቡን የሚጠቅሙ ሃሳቦችን በማፍለቅ ለተግባራዊነቱም በመረባረብ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የህዝቡን ለውጥ ማስቀጠል የማይችሉ አመራሮችን በመለየትም አቅም ያላቸውና ከለውጥ ማዕበሉ ጋር መራመድ የሚችሉ አዳዲስ አመራሮችን ለማምጣትም እየተሰራ ነው። በአማራ ተወላጆችም ሆነ በሌሎች ህዝቦች እየተስተዋለ ያለው መፈናቀልም ባለፉት ጊዜያት የተበተነው መጥፎ  የፖለቲካ  ዘር እንደሆነ አመልክተው፤ "ይህን በዘላቂነት ማስቆም የሚቻለውም ሁሉም አግላይ የሆነውን አስተሳሰብ መንቀል ሲቻል ብቻ ነው "ብለዋል። እንደ አቶ ገዱ ገለጻ የክልሉ ህዝብ የልማት ፍላጎት  መሰረት ያደረገና የገንዘብ አቅምን በማገናዘብ የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎችም የልማት ስራዎችን በእኩልነት ለማልማት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው። "ምሁራን ለውጡ ግቡን እንደመታና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የተሳሳትነውን አርሙ፣ ከጎናችን ተሰለፉና አብረን እንስራ " ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል መምህር ተሻገር ወልደጊወርጊስ በሰጡት አስተያየት በውይይቱ የለውጡ ባለቤት ሁላቸውም እንደሆኑና  ይህንንም  ለማስቀጠል ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ መገንዘባቸውን ተናግረዋል። " የለውጡ ባለቤት እኛ ነን"  ያሉት መምህሩ ለውጡ በማንኛውም መንገድ እንዳይደናቀፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል። ሃገርን ከውድመትና ከውድቀት ለማዳን የምሁራን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ በተሰማሩበት የማስተማር ስራ ለውጡን እያሰቡ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ መምህር ኃይለየሱስ ገዳሙ ናቸው። የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከርዕሰ መስተዳደሩ ጋር ባደረጉት ውይይትም ክልላዊና ሃገራዊ ወቅታዊ ጥያቄዎች  ተነስተው ምላሽ ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም