የመጣው የለውጥ እድል ባኮረፉ ኃይሎች አማካኝነት እንዳያመልጠን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል -ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ

158
አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2010 በኢትዮጵያ የመጣው የለውጥ እድል ባኮረፉ ኃይሎች አማካኝነት እንዳያመልጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ገለጹ። ቀደም ባሉት ዘመናት የአገሪቱን ታሪክ ሊቀይሩ የሚችሉ በርካታ ፖለቲካዊ አጋጣሚዎች ቢኖሩም እድሉን በጥንቃቄ መጠቀም ባለመቻሉ መምከናቸውን አስታውሰዋል። ዶክተር ዳኛቸው በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የመጣውን አይነት ለውጥ ሲመጣ የሚያኮርፉ ኃይሎች በየትኛውም ስርዓት መኖራቸው አይቀርም። ለውጡን በመቃረን የሚያኮርፉ ሃይሎች ለውጡን በመቃረን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመጣውን የለውጥ ዕድል እንዳያመክኑ ለመከላከል ሁሉም በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በርካታ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ያሏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር እንደመግባታቸው የሀሳብ ልዩነትን እንደ እድል በመቁጠር መንግስት ሰፊ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት እንዳለበትም ጠቁመዋል። ፖለቲካ የሚዳብረው በውይይት በመሆኑ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት ተከብሮ ልዩነትን ያልዘነጋ፣ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ወደፊት ተሰባስበው ግንባር የሚፈጥሩበት ሁኔታ ይኖራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸው ለዚህ መንግሰት ምቹ መደላደል መፍጠር የሚጠበቅበት መሆኑን ጠቁመዋል። ፖለቲካ የሚፈልገውን ውይይት በስፋት ለማካሄድ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የተለያዩ ሃሳቦችን ማስተናገድ ተገቢነት እንዳለውም ጠቅሰዋል። በዲሞክራሲ ስርዓት የሲቪል ማህበራት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ በተፎካካሪዎች ቅሬታ የሚነሳበት ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ለህግ የበላይነት መከበር የሚሰሩ ተቋማት ነፃ ሆነው መቋቋም እንዳለባቸው ተናግረዋል። የሲቪል ሶሳይቲ ለህግ የበላይነት መጠበቅ ወሳኝ ተቋማት በመሆናቸው በአዲስ መልክ ተስተካክለው መቀረጽ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም