በሀገሪቱ በምርት ዘመኑ ከዋና ዋና ሰብሎች 375ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል

88
ደብረብርሃን ነሀሴ 5/2010 በኢትዮጵያ በ2010/2011 የምርት ዘመን  ከዋና ዋና  ሰብሎች 375 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ  ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚስቴር መስሪያ ቤቱ  የ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የቀጣዩ ዘመን  እቅድ ዝግጅት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደብረብርሃን ከተማ የውይይት መድረክ አካሄዳል። በሚስቴሩ የሰብል ልማት ዳሪክቶሬት ከፍተኛ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ስብሃት ተመስገን በመድረኩ እንዳሉት ምርቱን ለመሰብሰብ የታቀደው 13 ሚሊየን ሄክታር  መሬት በማልማት ነው። በዚህም 375 ሚሊየን ኩንታል ከዋና ዋና  የምርት ሰብሎች ለመሰብሰብ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም እንዲሁም የተባይና የአረም ማስወገድ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። ከሚጠበቀው ከዚሁ ምርት ውስጥ  ከሁለት ሚሊዮን  ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንደሚሆን አመልክተዋል። በምርት ዘመኑ የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግም ከአንድ ሚሊዮን 700ሺህ በላይ የአፈር ማዳበሪያ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ ነው። አሁን ያለው የአርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ፍላጎት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ15 በመቶ ማደጉን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ በየሮ በበኩላቸው " በምርት ዘመኑ በግብዓት አቅርቦት ስራ ላይ የተነሱ የትራንስፖርት ችግሮች በቀጣይ እንዳይደገም ይሰራል "ብለዋል በግብዓት አቅርቦቱ 27መርከቦች መሳተፋቸውን ጠቁመው ሁሉም በአንድ ወቅት ወደብ ሲደርሱ ወደ መሃል ሀገር በሚደረገው የማጓጓዝ ስራ ፣ የመጋዘንና የአውራጅ ጫኝ ችግሮች ተከስተው እንደነበር አውስተዋል። ማዳበሪያ ወደብ ከደረሰ በኋላ መጉላላት እንዳይፈጠር መቀበልና በፍጥነት የማስገባት  ስራው በእቅድ በመምራት  ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ሌላው ተሳታፊ የደቡበ ምርጥ ዘር ድርጅት ስራ አስኪያጀ አቶ በላይ ሀሪሶ እንደገለጹት ምርታማነትን ለማሳደግ ግብአት ወሳኝ በመሆኑ በተያዘው  ዓመት የበቆሎ እና ስንዴ ምርጥ ዘር ከ90ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለቀጣዩ የምርት ወቅትም በ7ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የዘር ብዜት በማካሄድ 150ሺህ ኩንታል የተለያየ የሰብል ምርጥ ዘር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ለሁለት ቀናት የተካሄደውና ትናንት በተጠናቀቀው የውይይት መድረክ ባለፈው በጀት ዓመት የነበሩ ክፍተቶችን በቀጣይ በማስተካካል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገበ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ የግብርና ምርምር ተቋማት፣ የፌዴራልና  የየክልሉ ባለድርሻ አካላት በውይይት መድረኩ ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም