በደቡብ ክልል የጌዲኦ ዞን ምክር ቤት የአምስት የካቢኔ አባላትን ሹመት አጸደቀ

97
ዲላ ነሀሴ 5/2010 በደቡብ ክልል የጌዲኦ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው አስቸኳይ ጉባኤው የዞኑን የ2011 በጀት ከ1ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን አጸደቀ። ምክር ቤቱ ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ጉባኤ የአምስት የካቢኔ አባላትን ሹመትና ሌሎች ውሳኔዎችንም አፅድቋል ፡፡ የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት በ4ኛ ዙር 4ኛ አስቸኳይ ጉባኤው ለ2011 ካጸደቀው የአንድ ቢሊዮን 323 ሚሊዮን 847 ሺህ 350 ብር በጀት ውስጥ ለዞን መደበኛና ካፒታል በጀት 149 ሚሊዮን 804 ሺህ 856 ብር መድቧል። ከዚህ በተጨማሪም ለዞናዊ ፕሮግራሞች 138 ሚሊዮን 13 ሺህ 924 ብር ፤ ለመጠባበቂያ በጀት 18 ሚሊዮን 723 ሺህ 189 ብር እንደሁም ለወረዳዎችና ከተሞች አንድ ቢሊዮን 17 ሚሊዮን 305 ሺህ 381 ብር ምክር ቤቱ መድቧል። የበጀት ምንጩም ከመንግስት ግመጃ ቤት ፤ ከዞናዊ ገቢ ፤ ከድጎማ እንዲሁም ከጤና ተቋማት ፤ ከትምህርት ተቋማትና ከማዘጋጃ ቤቶች የሚሰበሰብ መሆኑን ተመልክቷል። ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ የቀረቡለትን አምስት የካቢኔ አባላት ሹመት አጽድቋል። በአምስት የተለያዩ የመንግስት ሥራ አስፈፃሚነት ቦታዎች ላይ በዞኑ ዋና አስተደዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ አቅራቢነት የካቢኔዎችን ሹመት አፅድቋል ፡፡ በዚህም መሰረት 1ኛ አቶ ተካልኝ ታደሰ የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ 2ኛ አቶ ተወልደ ተስፋዬ የጌዴኦ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ 3ኛ አቶ ዳንኤል ስዩም የጌዴኦ ዞን ፀጥታና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ 4ኛ አቶ ከፊያለው ገመዴ የጌዴኦ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም 5ኛ ወይዘሮ ሰናይት ጅግሶ የጌዴኦ ዞን ሴቶችና ሕጻናት መምሪያ ኃላፊነት  ሹመትን በማጽደቅ ጉባኤውን አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም