በሶማሌ ክልል በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሚወገዝ ተግባር ነው -የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች

67
አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2010 በሶማሌ ክልል በአብያተ ቤተክርስቲያናት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ተቀባይነት የሌለውና የሚወገዝ መሆኑን የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች ገለጹ። ድርጊቱ እንዳይደገም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም መሪዎቹ አረጋግጠዋል። በሶማሌ ክልል በቅርቡ በተፈጠረው አለመረጋጋት የሰዎች ህይወት ሲያልፍ የንብረት ውድመትም ደርሷል። ለአብነትም ከሰባት በላይ አብያተ ቤተክርስቲያናት የተቃጠሉ ሲሆን አገልጋይ ካህናትም ህይወታቸው አልፏል። በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች እንደገለጹት፤ ድርጊቱ ከእምነት ሰዎች ውጪ የተደረገና የተወገዘ ነው። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዑዝታዝ አቡበከር አህመድ የእስልምና እምነት አንድን ንጹህ ነፍስ ማጥፋት የዓለም ህዝብ ማጥፋት እንደሆነና የሰው ህይወት ማጥፋት የተወገዘ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል። በጂግጂጋ የተፈጸመው ትልቅ በደል እንደሆነ ተናግረው ''ዜጎች በአገራቸው ነጻነት አግኝተው የፈለጉትን አምልከው መኖር የሚችሉትበት አገር ላይ በብሄራቸውና በእምነታቸው ሳቢያ ጥቃት መፈጸም እምነትን አይወክልም የእምነትም ሥራ አይደለም'' ብለዋል። የትኛውም ቦታ ላይ እንደዚህ አይነት ተግባራት ሲፈጸሙ የሚያዪ አማኞች ሁሉ እምነታቸውን ስለማይወክል ድርጊቱን በማውገዝና የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎችን ለሕግ አሳልፈው መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የእምነቱ ተከታዮችን ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረትም መደገፍ እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል። እንደ ሙስሊም ማህበረሰብ ተወካይነታችን በየአካቢው ሙስሊሙ ማህበረሰብና አስፈጻሚ አካላት መምህራንና ተቋማት ለህዝቡ ይህንን መልዕክት እንዲያስተላልፉና ህዝቡ ትክክለኛውን መስመር እንዲከተሉ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። ''እኛም እንደ አስፈላጊነቱ በየአካቢው በመሄድ አማኞች መሰል ድርጊቶች ላይ እንዳይሳተፉና እንዲያወግዙ የማስተማር ኃላፊናታችንን እንወጣለን'' ሲሉም አረጋግጠዋል። የታላቁ አንዋር መስኪድ ኢማም ሼህ ጣሃ መሐመድ በበኩላቸው በሱማሌ ክልል በክርስትያን ወንድሞች ላይ የተፈጸመው ጥቃት እምነቱን የማይወክል ከመሆኑም በላይ የሰው ልጅ የሚፈጽመው ተግባር አይደለም። መሰል ድርጊቶች እንዳይደገሙ ስለ ሠላም በተለያዩ መንገዶች የማስተማርና የማስገንዘብ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። ''በተለይ ወጣቶች በሌላው አካል ላይ ጉዳት እንዲደድርስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መስማት የለባቸውም''ያሉት ኢማሙ መጥፎ ነገር ማድረግ በፈጣሪም ዘንድ እንደሚያስጠይቅ ምክር እየሰጠን ብለዋል። ሼህ አህመድ ኢብራሂም የተባሉ የኃይማኖቱ አባት ''ከኛ በፊት የነበሩ መሪዎች በአንድነት መኖርን ነው ያስተማሩን'' ሲሉ በመግለጽ የተፈጸመው ድርጊት የሚወገዝ መሆኑን ገልጸዋል። ''ሙስሊምና ክርስቲያን በችግር ግዜ በመደጋገፍ ነው የሚታወቁት'' ያሉት ሼህ አህመድ አሁንም በሁለቱ የእምነት ተከታዮች ዘንድ ይሄ መተሳሰብ እንዲቀጥል ትምህርት በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም