ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ተሳታፊ ወጣቶች በመቀሌ ወደ ስራ ተሰማሩ

49
መቀሌ ነሀሴ 5/2010 በመቀሌ ከተማ የተሰማሩት ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ተሳታፊ ወጣቶች የሰላም፣ የአንድነትና የልማት አምባሳደሮች ሆነው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ። በከተማው ከትናንተ ጀምሮ  ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ተመራቂው  አህመድ እንድሪስ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት የትግራይ ህዝብ ባህልና ወግ፣ታሪክና ማንነት ለማየትና ለማወቅ ፍላጎት እንደነበረው ተናግሯል። በመቀሌ  ሰማእታት ሃወልት የሚገኙ የህወሓትና የትግራይ ህዝብ ታሪክና ቅርስ ጎብኝቶ በተሰራው ታሪክ መደነቁንም ገልጾል። ከተሰማሩበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፅዳት አንዱ መሆኑ ገልፆ፤ በሰማእታት ሃወልት ውስጥ ለውስጥ የማፅዳት ስራ መጀመራቸውም ተናግሯል። የሶስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ አማኑኤል ሃይለስላሰ በበኩሉ ለ15 ቀናት በሚያደርጉት ቆይታ ደም በመለገስ ፣ ችግኝ በመትከልና በአካባቢ ጽዳት ተሰማርተው  አርአያ ለመሆን ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልጿል። " ህዝባችንን ለማየትና ነፃ አገልግሎት ለመስጠት ነው የመጣነው፤ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ስራ በመጀመራችንም የመንፈስ እርካታ ሰጥቶናል " ያለችው ደግሞ የኢኮኖሚክስ ተመራቂ ነፃነት ኃይላይ ናት። የልማት ስራዎች  ከማካሄድ ሰሰላምና አንድነት እንደሚሰብኩም ተናግራለች። የሀገሪቱን ሰላም፣ አንድነትና ልማት እንዲጠናክር  አምባሳደሮች ሆነው በመንቀሳቀስ የድርሻቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት በተግባር በማሳየት እንደሚገፉበት አሰተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ነጋ አሰፋ ለወጣቶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ አቶ ነጋ በዚሁ መልዕክታቸው " የወጣቶች ሁለንተናዊ ጥቅም የሚረጋገጥባት ሀገር ማድረግ የሚቻለው በወጣቱ የተቀናጀ ሰላማዊ ትግል መሆን አለበት" ብሏል። ሰላማዊ ትግል ማካሄድ የሚቻለው ደግሞ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  አንድነት ያረጋገጠ የፌዴራል ስርዓት በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል። የወሳን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ተሳታፊ ወጣቶች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጓዳኝ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር መስራትና  ውጤታማ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም