የቀድሞዋን ጅግጅጋ ናፍቆት

94
ሃና ከበደ ትባላለች፡፡ ከዛሬ 12 ዓመት በፊት ነበር በወሎዋ ቆቦ ከተማ በአነስተኛ ንግድ ያፈራቻትን ወረት ይዛ ወደ ጅግጅጋ ያቀናችው፡፡ ጅግጅጋም ሃናን እንደ ባይተዋር ሳይሆን እንደ ወላድ አቅፍ ድግፍ አድርጋ ለማሳደግ በደስታ ተቀበለቻት፡፡ ልጆቿም አንቺ የከሌ ወገን ነሽ የኛ አይደለሽም ሳይሉ ፍቅርን ለገሷት፡፡ ሃናም በፍቅር በተቀበለቻት ጅግጅጋ ያላትን እየሰጠች ቀሪውን ደግሞ በብድር እያመጣች የልብስ መደብር ከፈተች፡፡ ካሰበችው በላይ ስራው አልጋ በአልጋ የሆነላት ሃና የከፈተችው ሱቅ ትርፋማ አደረጋት፡፡ ከእለት ጉርሷ የተረፈው ገቢዋም በከተማው መኖሪያ ቤት እንድትገነባ አስቻላት፡፡ ሃና በጊዜው በምትኖርበት አካባቢ የነበረውን ፍቅር እንዲህ ታስታውሰዋለች፡፡

ኑሮ በጣም አሪፍ ነበር። ሁሉ ነገር በጣም ጥሩ ነበረ።ኑሮም አሪፍ ነው ርካሽ ነው እንዲህም አልተወደደም ሰውም ጥሩ ነበር አይደል ከ12 ዓመት በፊት ከሶስት ዓመት ራሱ በጣም አሪፍ ነበረ። አሁንም እዛም ውስጥ ሆኖ የማይፈልግ አለ ይህን ነገር። እኛንም ያዳኑን እነሱ ናቸው ሶማሌዎች። መጥፎም እንዳለ ጥሩም አለ፤ እና እንዲህ ነበረ እዛ ውስጥ።

ይህን በደስታና ፍቅር የተሞላ ማሕበራዊ መስተጋብር እያጣጣመች ባለችበት ወቅት ጅግጂጋ ሌላ ደስታ ትሸምት ዘንድ የኔ የምትለውን የትዳር አጋር አከለችላት፡፡ ትዳሯም ወዲያው በወንድ ልጅ ተባረከ፡፡ በተለይ ልጇን በምትወልድበት ወቅት የሶማሌ ክልል ተወላጁ የቀድሞ አከራይዋና ሌሎች መሰል ጎረቤቶቿ ያደረጉላትን እንዲህ ትናገራለች፡፡

እና የሚገርምህ ስወልድ ራሱ እነሱ ናቸው ያረሱኝ። ቤተሰቦቼ በጣም እሩቅ ናቸው አያውቁትም ባህሉን የእዚህን አገር የሆነ ይቀላቀልባቸዋል እና እነሱ ናቸው ያረሱኝ። እና አሪፍ ነበረ፡፡

ዛሬ  ሃና እንዲህ በፍቅር ያኖረቻት ጅግጂጋ ፊቷን አዙራባት፤ ያፈራችውን ንብረት ተቀምታ ፤ ከሞቀ ጎጆዋ ተፈናቅላ በሀረር ከተማ  ትምህርት ቤት ተጠልላለች፡፡ ሌላው ቢቀር ለፍታ ካፈራችው ገንዘብ የመጓጓዣ እንኳ ሳይሆናት ቀርቶ  ከጂግጂጋ ሃረር ከተዘረጋው ኪሎሚትር  ወስጥ ጥቂት የማይባለውን በሌሊት በእግሮቿ ተጉዛለች፡፡ ሃና የአራት ወር ነፍሰ ጡር ስትሆን በጅግጅጋ በተፈጠረው ግርግር ንብረቷን ከማጣቷ ባሻገር ዘራፊዎቹ እኩይ ምግባራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ህይወቷን ለማጥፋት በተኮሱት ጥይት እጇ ጉዳት ደርሶበታል፡፡

 አንዱ ተኮሰብኝ። እንግዲህ ሆዴንም የፈለገበት ቦታ መምታት ይችል ነበር እግዚአብሄር ሲያድነኝ ነው እንጂ። ሲተኩስብኝ እንዲ እጄን ወደ ላይ አንስቼ ነበር እራሴን ስከላከል በዚህ ገብቶ ወጣ። ወጥቶ እንግዲህ የሆነ የእኔ ቢጤ ነው የነበረው እሱን ገደለው ጭንቅላቱን ነው የመታው። ሰው ይገሉ ነበር ንብረት ያቃጥሉ ነበር።

ይህቺ ነፍሰ ጡር እንስት በጥይት ተመታ ሐረር እስክትደርስ ድረስ ምንም አይነት ህክምና ሳታገኝ የተጎዳውን እጇን በጨርቅ አስራ ደም እየፈሰሳት አምስት የሲቃ ቀናቶችን ሌሊቶችን እንዳሳለፈች አጫውታናለች፡፡ ሃና በጅግጂጋ በተከሰተው ሁከት የተለያዩ ግለሰቦችን ንብረት ማውደምና ሕይወትን በአሰቃቂ ሁኔታ እስከ ማጥፋት የደረሱ ተግባራትን ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦችን ብትመለከትም፤ በተቃራኒው በቤቶቻቸው ኮርኔስና መኝታ ቤት በርካታ ሰዎችን ደብቀው ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸው አስከፊ አደጋ እንዳይደርስባቸው የታደጉ የአገሬው ተወላጆች እንደነበሩም ትናገራለች፡፡ የእርሷ የቀድሞ አከራይ ምንም አይነት ጎሳ፣ ዘር፣ ብሄር ሳይለይ እርሷን ጨምሮ ያገኛቸውን ሌሎች 30 ግለሰቦችን በቤቱ ደብቆ መታደጉንም ለአብነት አንስታልናለች፡፡

ያ ሰውዬ ነው እኛን መጥቶ ያዳነን ታከሲ ያለ ምንም እንትን ቤቱ ድረስ ይዞን የሄደው ወደ 30 ሰው አማራ ኦሮሞ ትግሬ ሳይል በብሄር አልነበረም የሚገርምህ 30ዎቻችንም ብሔራችን ይለያይ ነበረ።

የመጀመሪያ ልጇ ትምህርት ቤት በመዘጋቱ ምክንያት የአባቱን ዘመዶች ለመጠየቅ ከተፈጠረው ሁከት በፊት አስቀድሞ ወደ ድሬዳዋ እንደሄደ የምትናገረው ሃና፤ ባለቤቷ ግን እስካሁን የት እንዳለ አታውቅም፡፡ ሁከቱ በተፈጠረበት ወቅት እርሱም እንደመሰል ተፈናቃዮች አካባቢውን ለቆ እንደወጣ ሐረር መጥታ ሰዎች እንደነገሯት አጫውታናለች፡፡ ሐና ከጅግጅጋ ውጭ የትም መኖር እንደማትፈልግ የነገረችን ሲሆን፤ ከ12 ዓመት በፊት እርሷ በምታውቃት ጅግጅጋ ተመልሳ  በደስታና በሰላም የምትኖርበትን ቀን  አሻግራ ትናፍቃለች፡፡ "አሁን የተፈጠረው ነገር ጅግጅጋን አይገልጻትም" የምትለው ሃና፤  ሰሞኑን የተፈጠረው ሁከት ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር ከንቱ መሆኑን መረዳቷን ትናገራለች፡፡ በተለይ የቀድሞው ሰላማችን እንዲመለስ እንዲህ አደረጉን ከሚለው ውንጀላ ወጥተን ወደፊት ብቻ መመልከት ይገባል ስትልም ምክሯን ለግሻለች፡፡

ወደ ፊት ሰላም ተፈጥሮ አንድ ላይ በዱሮ ጂግጂጋ የዱሮ አገራችን ሆና እኔም የትም አልሄድም በጣም ስለምወዳቸው ማለት ነው። የሌላውን አላውቅም እኔ እነደዛ ቢሆን ደስ ነው የሚለኝ ያለንን ተቋድሰን በልተን ብሄር ሳንለይ ትናንት እንዲህ አድርገውናል ወደ ኃላ ሳንመለስ ሌላ ማንነታችንን ይዘን ብንኖር እኔ ደስ ነው የሚለኝ። ትናንት አቃጥለውናል፣ ቤት አቃጥለውብናል በመሳሪያ ተመተናል ያ አይደለም ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው።

ሰላም ለኢትዮጵያ !ሰላም ለአፍሪካ! ሰላም ለዓለም!
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም