በክልሉ በጤና ተቋማት የሚስተዋለው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ችግር ለመፍታት መስራት ይገባል--- አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

69
ባህርዳር ነሀሴ 5/2010 በጤና ተቋማት የሚስተዋለው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ችግር ለመፍታት አመራሩና የጤና ባለሙያዎች በባለቤትነተ ሊሰሩ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ። ሁለተኛው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የንቅናቄና የዕውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም ተካሂዷል። ርዕሰ መስተዳደሩ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ስነስርዓት ወቅት እንደተናገሩት የጤና ተቋማት በክልሉ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የህብረተሰቡ የመገልገል ፍላጎት እየጨመረ ነው። ለዚህ ደግሞ በ2010 በጀት ዓመት ብቻ አጠቃላይ ወደ ጤና ተቋማት ሄዶ አገልግሎቱን ያገኘው ህዝብ ቁጥር 24 ሚሊዮን መድረሱን በመጥቀስ፡፡ በተለይ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራም ህብረተሰቡ  ታቅፎ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን አባላትን በማፍራት በኩል እየተከናወነ ያለው ስራ አበረታች ነው። በፕሮግራሙ በአባልነት የታቀፉ አርሶ አደሮች ገንዘብ ከፍለው እያለ በሚፈለገው ልክ ተገቢውን አገልግሎት የማያገኙበት ሁኔታ እንደሚስተዋል አቶ ገዱ አመልክተዋል። በክልሉ ጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በመሰረታዊነት ለመፍታት የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ጋሻው በበኩላቸው ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለሁሉም የክልሉ ህዝብ በፍትሃዊነት ለማዳረስ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግቡን ለማሳካትም በክልሉ በ2001 ዓ.ም በሶስት ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮግራም አሁን ላይ ወደ 156 ወረዳዎች ተስፋፍቷል። በፕሮግራሙ ሁለት ሚሊዮን 200ሺህ አባወራዎችን አባል በማድረግም ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ከ10 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በፕሮግራሙ ከታቀፉ  አባላትም በዓመቱ 600 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ማሰባሰብ መቻሉን የጠቆሙት አቶ ብዙአየሁ "800 የሚሆኑ የጤና ተቋማትም ውል ይዘው አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛሉ" ብለዋል። በዘርፉ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻልም ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታና የግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም የአሰራር ማሻሻያ ደንብና መመሪያዎች ወጥተው ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በተያዘው የበጀት ዓመትም ቀሪ 24 ወረዳዎችን በመሸፈን ህብረተሰቡን የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚከናወን አስታውቀዋል። " ህዝቡ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በመስራታችን የመኪና ተሸላሚ እንድንሆን አስችሎናል" ያሉት ደግሞ የምስራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታነህ ታደሰ ናቸው። የተሰጣቸው ሽልማት በቀጣይም የተሻለ ሰርተው ህብረተሰቡን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን  ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እንደሚያነሳሳቸውም ተናግረዋል። ከሰሜን ወሎ ዞን ሃብሩ ወረዳ የአንጦ ጤና ኬላ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሪት የሺ ሞላ በበኩሏ የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጁን የተሻለ መፈፀሟና አርሶ አደሩ የጤና መድህን አባል  እንዲሆን በመስራቷ ለሽልማት መብቃቷን ገልጻለች። " ያገኘሁት ሽልማት በቀጣይ ይበልጥ ጠንክሬ በመስራት ህብረተሰቡን እንዳገለግል ተጨማሪ አቅም ይሆነኛል "ብላለች። በባህርዳር ከተማ  ትናንት በተከናወነው የዕውቅና አሰጣጥ ስነሰርዓት ወቅት ለጤናው ዘርፍ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ 97 ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም