በህገወጥ መንገድ የተገኘ ስኳርና ልባሽ ጨርቅ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በህገወጥ መንገድ የተገኘ ስኳርና ልባሽ ጨርቅ ተያዘ
62
አዳማ ሀምሌ 5/2010 ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት ስኳርና ልባሽ ጨርቅ መያዙን በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በተገባደደው ሳምንት የተለያዩ ቀናት በህበረተሰቡ ጥቆማ ከተያዘው መካከል ስኳሩ 75 ኩንታል መሆኑን በጽህፈት ቤቱ የህግ ማስከበር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሀኑ ለታ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ መንግስት ለህብረተሰብ እንዲከፋፈል የላከው ይሄው ስኳር ከአዳማ ወደ አፋር ክልል መጓዝ ሲገባው የጫነው ተሽከርካሪ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሌ ከተማ በመግታት አራግፎ ለመሸጥ ሲሞከር ሊያዝ ችሏል። እንዲሁም በኮንትሮባንድ በሞያሌ በኩል ሀገር ውስጥ የገባ 90 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ ደግሞ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-45684አ.አ. በሆነ ኤፍ ኤስ አር የተሽከርካሪ ተጭኖ ከሻሸመኔ ሞጆ ከተማ እንደደረሰ በፌዴራል ፖሊስና በአዳማ ጉምሩክ ህግ ማስከበር አባላት ክትትል ተይዟል፡፡ በተጨማሪም ነሐሴ 2 /2010ዓ.ም. የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-22854አ.አ. በሆነ ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ የተጫነ 91 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ አሰላ ከተማ እንደደረሰ በፖሊስ ተይዞ ለጉምሩክ ገቢ መደረጉን አቶ ብርሀኑ ገልጸዋል። በሀገ ወጥ መንገድ የተገኘው ስኳርና ልባሽ ጨርቁ ግማሽ ሚሊየን ብር እንደሚገመት ጠቁመው እነዚህን ጭነው የተገኙት የአንደኛው ተሽከርካሪ ሾፌርና ረዳቱ መያዛቸውና የሌላው አሸከርካሪ ንብረቱን ጥለው መሰወራቸውን አመልክተዋል፡፡ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ህብረተሰቡ አጥፊዎችን በመጠቆም እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጠል አስተባባሪው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።