የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የጥላቻን ግንብ የምናፈርስበት ነው—የበጎ ፍቃድ ተሳታፊ ወጣቶች

880

አምቦ / ጎባ ነሃሴ 4/2010 የወሰን ተሸጋሪ በጎ ፍቃድ አገልግሎት የጥላቻን ግንብ በማፍረስ የፍቅር ድልድይን ለመገንባት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን የመጡ ወጣቶች ገለጹ፡፡

የጊኒር ወረዳ ወጣቶች በበኩላቸው በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ በተጠናከረ መልኩ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን ለመጡ የአገሪቱ ወጣቶች አቀባበል ተደርጓል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ወጣቶች መካከል ከደቡብ ክልል የመጣው ወጣት መለሰ ጴጥሮስ እንዳለው ጥላቻን አስወግዶ ፍቅርን በተግባር ለማሳየት ወደአካባቢው መምጣቱን ተናግሯል።፡

በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራው የአካባቢውን ህብረተሰብ በትምህርት ዘርፍ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ጎን ለጎንም በምዕራብ ሸዋ ዞን አካባቢ የህብረተሰቡን አኗኗርና ባህል ለመቅሰም መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡

ከትግራይ ክልል የመጣችው ወጣት ብረይ ኃለፎም በበኩሏ በወሰን ተሸጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ለማድረግ ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን እንደመጣች ተናግራለች፡፡

የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱም ትልቅ አገራዊ ኃላፊነትን የምትወጣበት በመሆኑ ደስተኛ መሆኗን ገልጻ፣ ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ ወደሌላ አካባቢ ሄዳ አገልግሎት መስጠቷ ፍቅርና አንድነትን ለመገንባት ዕድል እንደሚሰጣት ገልጻለች።

አገሪቷ በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ይህን ማህበራዊ አገልግሎት ለመስጠት በመምጣትዋ መደሰቷን የገለጸችው ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የመጣችው ወጣች አየለች ተሾመ ናት።

በምትሰጠው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሄደችበት ማህበረሰብ ጋር ግንኝነቷን በማጠናከር የፍቅር ድልድይን ለመገንባት የሚያስችላትና ለእዚህም ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡

በወሰን ተሸጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች የአቀባበል ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የአምቦ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ቢቂልቱ ከተማ በበኩላቸው ወጣቶቹ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ለዞኑ ልማት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ወጣቶቹ በቆይታቸው ለህበረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመስጠት ጎን ለጎን ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ልምድ መለዋወጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰፋዬ ጎሶምሳ ወደ ዞኑ የመጡት 125 ወጣቶች ለ15 ቀናት በጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ በቆይታቸው በደም ልገሳ፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ አቅመ ደካሞችን በመርዳትና በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ እንደሚሳተፉ አመላክተዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የጊኒር ወረዳ ወጣቶች በበኩላቸው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ በተጠናከረ መልኩ እያከናወኑ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ እስካሁን ድረስ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የልማት ሥራዎች ማከናወናቸውም ተገልጿል።

በዞኑ ጊኒር ወረዳ ነዋሪና የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ 2ኛ ዓመት ተማሪ ወጣት ከድር አማን በአካባቢያቸው ለሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል።

“በክረምቱ ወጣቶች ተሰባስበን ደም ለግሰናል፤ የከተማ ጽዳት ሥራም አከናውነናል፤ ይህ የክረምት በጎ ፍቃድ ሥራ ወጣቱን በተለያየ የልማት ሥራ ላይ እንዲሳተፍ ስለሚያደርግ ወደፊት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብሏል።

ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በኢንቫይሮሜንታል ሄልዝ የተመረቀው ወጣት አብዱሰመድ ጀማል በበኩሉ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን የአቅመ ደካማ ሰዎችን መኖሪያ ቤት እያደሱና እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

“አገልግሎቱ ወጣቱ ኃይል በአገር ልማት ውስጥ የራሱን አሻራ እንዲያኖር እድል የሚፈጥር በመሆኑ በተቀናጀ መልኩ መጠናከር ይኖርበታል “ብሏል፡፡

“በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በፖለቲካል ሳይንስና በግጭት አፈታት እሳቤ ላይ የቀሰሙትን ዕውቀት ለህብረተሰቡ በመስጠት ላይ ነን” ያለው ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተማሪ አብዲሳ አዱኛ ነው ፡፡

“በሰላሙ ዙሪያ የሚሰጠው ትምህርት ማህበረሰቡ ሰላሙን በመጠበቅ የተጀመሩ አገራዊ ለውጦችን እንዲደግፍ ለማስቻል ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል” ብሏል፡፡

የባሌ ዞን የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣፋ በበኩላቸው ዘንድሮ ለሁለት ወራት በሚቆየው የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራ በዞኑ ከ145 ሺህ 500 በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው በሚሰጡት አገልግሎትም 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት የልማት ሥራዎችን ያከናውናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

እስካሁንም ወጣቶች በስምንት ዋና ዋና የልማት መስኮች ባከናወኑት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ለማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በባሌ ዞን ባለፈው ዓመት በተከናወነው የወጣቶች የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሥራ በወጣቶች ተከናውኖ እንደነበር ከዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡