በቄለም ወለጋ በ13 ሺህ 400 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ የተከሰተ ተምች ተወገደ

68
ጊምቢ ነሃሴ 4/2010 በቄለም ወለጋ ዞኑ በ13 ሺህ 400 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ ተከስቶ የነበረው ተምች መወገዱን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ። የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ምንተስኖት አለሙ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በተያዘው የመኽር አዝመራ በዞኑ በተዘራ ከ14 ሺህ በላይ የበቆሎ ቡቃያ ላይ የአሜሪካ መጤ ተምች ተከስቶ ነበር። ተምቹ በሰብሉ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በተደረገው ርብርብ ከአንድ ሺህ ሊትር በላይ ፀረ ተባይ ኬሚካል መደኃኒት መረጨቱን ገልጸዋል። ተምቹን በኬሚካልና ባህላዊ ዘዴ ለመከላከል በተሰራው ስራ እስካሁን13 ሺህ 400 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ነጻ መሆኑን ገልጸዋል። ተምቹ በዞኑ በሚገኙ 11 ወረዳዎች መታየቱን የጠቆሙት ኃላፊው ተባዩን ለማጥፋት የተጀመረው እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። ተምቹን ለመከላከል በዋናነት ከ49 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን የበቆሎ ዘሩ በመስመር መዘራቱና ተቀናጅተው ርብርብ በማድረጋቸው የቁጥጥር ሥራው እንዲሳካ ካደረጉ ምክንያቶች የሚጠቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል። በዞኑ ተምቹ በስፋት ከታየባቸው ወረዳዎች መካከል ጊዳሚ፣ ላሎ ቅሌ፣ አንፊሎና ዳሌ ዋበራን ተጠቃሽ ናቸው። አቶ ቶለሳ ዲሳሳ የሰዮ ኖሌ ወረዳ ኦዶ ሶኮ ቀበሌ አርሶ አደር ሲሆኑ በዚህ አመት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ከዘሩት የቦቆሎ ቡቃያ በከፊል በተምቹ ተወሮ እንደነበር ተናግረዋል። ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር ተባብረው ተምቹን በለቀማ ለመከላከል ያከናወኑት ተግባር ምንም ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። በጊዳሚ ወረዳ ባታ ቀበሌ አርሶ አደር ጅባ ዱጉማ እንዳሉት አምና በቦቆሎ ማሳቸው ላይ የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች በአደራጃጀታቸው ተባብረው በመስራታቸው በሰብላቸው ላይ ጉዳት ሳይደርስ ለመከላከል መቻላቸውን አስታውሰዋል። "ከአምና ባገኘሁት ልምድ ተነስቼ ዘንድሮ ተምቹን በእጅ በመልቀምና አመድ በመጨመር የቦቆሎ ቡቃያዬን ከተምቹ መታደግ ችያለሁ" ብለዋል። በዞኑ በ2010/2011 የመኽር እርሻ በተለያዩ ዘሮች ከተሸፈነው 175 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 102 ሺህ ሄክታሩ በቦቆሎ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም