ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው መጠበቅ አለባቸው

71

ነሃሴ 14/2014 (ኢዜአ) ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው መጠበቅ እንዳለባቸው በመዲናዋ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ካሉ አስሩም ወረዳዎች የመጡ ወጣቶች ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን በሚመለከት ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች የሀገር ህልውናን በማስጠበቅ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ለሀገር ህልውና መጠበቅ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ወጣቶቹ ጥሪ ያቀረቡት።

ወጣት ዘገየ ወልዴ እንደሚለው፤ ወጣቶች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን ከመሆን ባሻገር የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው መጠበቅ አለባቸው።

ከዚህ አኳያ በክፍለ ከተማው የሚገኙ ወጣቶች በየአከባቢያቸው ካሉ ወረዳዎች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ነው ያነሳው።

ወጣት ፅጌ ድንቁ በበኩሏ ወጣቶች ሀገር እንድትቀጥል የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ትናገራለች።

ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው እየጠበቁ መሆኑንም ወጣቶቹ ተናግረዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ ፀጉረ ልውጦችንም ሆነ በገንዘብ ተደልለው የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን እኩይ ሴራ ለማስፈጸም የሚሰሩ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የጉለሌ ክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አባወይ ዮሃንስ ወጣቶች የሀገር ህልውናን ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ዜጎች በአንድነት በመቆም ሀገር የገጠማትን ችግር በጋራ መፍታት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸው ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቅ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም