በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ትውልድ ስፍራቸው ለመሄድ የትራንስፖርት ወጪ ተቸግረዋል

1011

ሐረር ነሃሴ 4/2010 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ትውልድ ስፍራቸው ለመሄድ የትራንስፖርት ገንዘብ አጥተው መቸገራቸውን ኢዜአ በሐረር ከተማ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ገለጹ።

የሐረሪ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ችግሩን ለመቅረፍ አስቸኳይ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት በርካታ ዜጎች ክልሉን ለቀው በሐረር ከተማ በሚገኘው መንፈሳዊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው ይገኛሉ።

የኢዜአ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ እንደታዘበው የከተማዋ ነዋሪዎች ለተፈናቃዮቹ በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ በማቅረብና አልባሳትን በመለገስ የወገን አልኝታነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ተፈናቃዮቹ በግጭቱ ምክንያት ክልሉን ለቀው ሲወጡ ገንዘብ ባለመያዛቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ የትራንስፖርት ወጪያቸውን ለመሸፈን እንደተቸገሩ ገልጸዋል።

ወጣት ቢኒያም አሽኮ ባለፉት ሦስት ዓመት በጅግጅጋ ከተማ በቀን ሥራ ተሰማርቶ ይኖር የነበረ ሲሆን በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር እስኪረጋጋ ድረስ ወደ ትውልድ ስፍራው ሆሳዕና መመለስ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

ሆኖም ግን ወደ ስፍራው ለመጓዝ የሚያስፈልገው የትራንስፖርት ክፍያ ስለሌለው እንደተቸገረም ገልጿል።

ሌላኛዋ ተፈናቃይ አዳነች ታደለ ወደ ትውልድ ቀየዋ ሁመራ መመለስ ፍላጎት ቢኖራትም በተመሳሳይ በትራንስፖርት ክፍያ ችግር እየተጉላላች መሆኗን ተናግራለች፡፡

የሐረሪ ክልል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር እንድሪስ በበኩላቸው ተፈናቃዮች የመጡት በድንገት ስለሆነ ተቀብሎ በማቆየት በኩል ቅንጅታዊ አሰራር አልነበረም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ የሚፈልጉ ተፈናቃዮችን የትራንስፖርት ወጪ በመቻል ሲያጓጉዙ መቆታቸውን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት በክልሉ አስቸኳይ ኮማንድ ፖስት የተቋቋመ ሲሆን ከነገ ነሐሴ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄድ ለሚፈልጉ ተፈናቃዮች የትራንስፖርት ክፍያ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ እስከሚወገድ ድረስ ወደ ትውልድ ስፍራቸውና ቤተሰቦቻቸው መመለስ ለማይፈልጉ ዜጎች በከተማዋ ጊዜያዊ የማቆያ ስፍራ እንደሚዘጋጁ አቶ ይመር ገልጸዋል፡፡