አገራዊ ለውጡ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም መንግስት ጥሪ አቀረበ

1091

አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2010 አገራዊ ለውጡ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም መንግስት ጥሪ አቀረበ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት በሳምንታዊ የመንግስት አቋም መግለጫው እንዳስታወቀው በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት እና በፍቅር እያሰባሰበ እና እያሳተፈ ነው።

የህዝቦችን የዓመታት ጥያቄዎች መመለስ እና ፍላጎቶችን ማሟላትን ታሳቢ አድርጎ በመካሄድ ላይ መሆኑንም መግለጫው ያትታል።

ለውጡ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና አንድነት፣ ዋስትና ላለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ጠንካራ መሰረት እየጣለ መሆኑ ተጠቅሷል።

ለውጡ የአፍሪካ አገሮችንና የጎረቤት አገራትን ጭምር ተጠቃሚ በማድረግ ዘላቂ ሰላም መፍጠርንና ቀጠናዊ ትስስርን ማጠናከርን ዓላማው አድርጎ በመንቀሳቀሱ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ ትላልቅ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎች መመዝገቡ ተጠቅሷል።

ይሁን እንጂ አገራዊ ለውጡ እንዲፋጠን እና የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ፣ የአገራችንን ሰላም መጠበቅ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት እና ተግባር ሊሆን ይገባል ተብሏል፡፡

መላው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በይቅርታ፣ ፍቅር፣ አንድነት እና የመደመር ጉዞ ላይ በመሆን የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ለአገሩ የሰላም ዘብ መሆኑን በተግባር እንዲያረጋግጥ መንግስት ጥሪውን አቅርቧል።

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።

ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ የአቋም መግለጫ- ነሐሴ 04 ቀን 2010 ዓ.ም.

 የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ለሰላማችን በህብረት ዘብ መቆም ይገባናል

በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገራት የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት እና በፍቅር እያሰባሰበ እና እያሳተፈ ያለ ለውጥ ነው።

 በቂም እና በቁርሾ ለዓመታት ተቃቅረው በኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል እርቅን ያወረደ፣ ለወደፊቷ ኢትዮጵያችን ዘላቂ ሰላም እና አንድነት፣ ዋስትና ላለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ እድገትና ብልጽግና መረጋገጥ፣ ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን እና ለመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ጠንካራ መሰረት እየጣለ ያለ ለውጥ ነው።

 ለውጡ በቅርብም ይሁን በሩቅ ያሉ የአፍሪካ አገሮችን ጭምር ተጠቃሚ ማድረግን ታሳቢ የሚያደርግ እንደመሆኑ ለዚህ አስፈላጊ የሆኑትን ከአካባቢ አገራት ጋር ዘላቂ ሰላም የመፍጠርን፣ መልካም ጉርብትናን እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን እንዲሁም ቀጠናዊ ትስስርን ማጠናከርን ዓላማው አድርጎ በመንቀሳቀሱ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ ትላልቅ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለ ነው፡፡

 ከለውጡ ዓላማ እና እንቅስቃሴዎች በመነሳትም የዓለም ኃያላን አገራት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ በተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁ አለም አቀፍ ተቋማትና የልማት አጋሮች፣ የፖለቲካ ተመራማሪዎች እና ጸሃፊዎችን እውቅና እና ድጋፍ አትርፏል፡፡

 በአጠቃላይ የተያያዝነው አገራዊ ለውጥ የህዝቦቻችንን የዓመታት ጥያቄዎች መመለስ እና ፍላጎቶቻችንን ማሟላትን ታሳቢ አድርጎ በመካሄድ ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በአንድነት እያሰባሰበ እና የተሻለች አገር ለመፍጠር በጋራ እያሰለፈ ያለ ታላቅ ለውጥ በመሆኑ ስኬታማነቱን ከወዲሁ መተንበይ ተችሏል፡፡

 ይሁን እንጂ አገራዊ ለውጡ እንዲፋጠን እና የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ፣ የአገራችንን ሰላም መጠበቅ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት እና ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተያያዝነው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመደመር ጉዞ ላይ ሆነን የምናካሂደውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል የአገራችን የሰላም ዘብ መሆናችንን በተግባር እንድናረጋግጥ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡