አዲስ የተሾሙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት አብረዋቸው እንዲሰሩ ጠየቁ

324
አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2010 አዲስ የተሾሙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ቀጣይ ለሚያከናውኗቸው ስራዎች ውጤታማነት ሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ከጎናቸው እንዲሆኑ ጠየቁ። ምክር ቤቱ ዛሬ ከሰዓት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ 18 የአዳዲስ የካቢኔ አባላት ሹመት፣ የአፈ ጉባኤና ሁለት የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ሹመት አጽድቋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው አዳዲስ የፍትህ፣ የቤቶች ልማት፣ የኢንዱስትሪና የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች የመዲናዋን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ፍሬህይወት ተፈራ እንደሚሉት በመዲናዋ ከፍትህ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የመልካም አስተዳድር ችግሮች ይነሳሉ። አሁን 'ፍትህ ለሁሉም' የሚለውን ሃሳብ መሰረት በማድረግ መነሻቸው የፍትሃዊነት ችግር የሆኑ የመልካም አስተዳደር እንከኖችን ለማስወገድ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ''ከሁሉም በላይ ለውጥ መጣ ሊባል የሚቻለው ሕብረተሰቡ የሚረካበትን ውጤት ማምጣት ሲቻል ነው'' የሚሉት ኃላፊዋ ዋና ዓላማቸው ለውጥ ማምጣት መሆኑን ተናግረዋል። በጥቅሉ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ከግብ እንዲደርስ በተለይ ባለድርሻ አካላት ከጎናቸው እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎችም ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል። የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ኢንጅነር ኤርሚያስ ኪሮስ ደግሞ የመጀመሪያ ስራቸው የሚሆነው በዘርፉ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መለየት እንደሆነ ተናግረዋል። ''ቀጣይ በአዲስ አስተሳሰብ ሙያዬን በመጠቀም ሕብረተሰቡን ማዕከል ያደረገና ያሳተፈ ስራ በመስራት ችግሮችን ለማቃለል እተጋለሁ'' ብለዋል። በዘርፉ ያሉ ችግሮች በአንድ ሰው ጥረት ሊፈቱ የማይችሉ በመሆናቸው ከሁሉም በላይ የከተማው ነዋሪና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እንዲደግፏቸው ይጠይቃሉ። 33 በመቶ ገደማ የሆነውን የመዲናዋ ወጣቶችን ሁሉን አቀፍ ችግሮች ለመፍታት በትጋት እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማሉ ጀምበር ናቸው። ኃላፊው እንደሚሉት ወጣቶች ከተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች ተቆጥበው ለከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከት የሚያስችሉ ስራዎች ቅድሚያ ያገኛሉ። ከዚህ በፊት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘረጉ አደረጃጀቶችና ፌዴሬሽኖችን በሙሉ አቅም ወደ ስራ ለማስገባትና የባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል። ሌላዋ የቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ኢንጀነር ሰናይት ዳምጠው ደግሞ የመዲናዋን ነዋሪዎች ከሚያስመርሩ ተግባራት መካከል የመኖሪያ ቤት እጥረት ዋነኛው መሆኑ እሙን ነው ይላሉ። ኢንጀነር ሰናይት ዜጎች የቤት ችግራቸው ተቃሎላቸው በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ፈጣን ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል። ሁሉም ተሿሚዎች የሚሰሩት ስራ በውጤት የታጀበ ይሆን ዘንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በሁሉም ዘርፍ ከጎናቸው እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም