ህይወታችንን ለማትረፍ ጫካ ስናቆራርጥ የተመለከትነው ግፍ እስከዛሬ እንቅልፍ ነስቶናል-- ተፈናቃዮች

93

ደሴ ነሀሴ 12/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ህይወታችንን ለማትረፍ ጫካ ለጫካ ስናቆራርጥ የተመለከትነው ግፍ እስከዛሬ እንቅልፍ ነስቶናል ሲሉ ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የተጠለሉ ወገኖች በምሬት ገልጸዋል ።

ኢዜአ ካነጋገራቸው ተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ አበባ ዘገዬ እንዳሉት የጥፋት ቡድኑ ሳያስቡት በከፈተባቸው ጦርነት ከራያ ቆቦ የሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ተጠልለዋል፡፡

ወይዘሮ አበባ  እንዳሉት በጥፋት ቡድኑ ድንገት ከተከፈተው ተኩስ ህይወታቸውን ለማትረፍ ነፍስ ያላወቁ አራት ህጻናት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ወልድያ ጉዞ ጀምረዋል ። ያውም ደግሞ የአንድ ዓመት ሕጻን ልጃቸውን በማዘል ።

ወይዘሮዋ ጫካ ለጫካ በማቆራረጥ በሚያደርጉት ጉዞ ገጠመኛቸውን ሲገልጹም "ልጆቼ ሲደክሙብኝ አሳርፋቸውና አባብላቸው ነበር፤ በየመንገዱ ነፍሰ ጡር ሴቶች ወድቀው አይቻለሁ፤ እንዲሁ  በጉዞ ድካም የወደቁ አዛውንቶችና በተባራሪ ጥይት ህይወታቸው ያለፈም ብዙ ነበሩ''።

"በየመንገዱ ደማቸውን እያዘሩ በስቃይ የወለዱ እናቶችንም ተመልክቻለሁ፣ ያ የተመለከትኩት ግፍና መከራ ትዝ እያለኝ እስከዛሬ እንቅልፍ ይነሳኛል " ሲሉ የቡድኑን አረመኔያዊ ተግባር ያስታውሳሉ።

እንደ እሳቸው ገለጻ ቡድኑ በደረሰበት ቦታ ሁሉ ወጣቶችን አፍኖ ይወስዳል፤ ሴቶችን ይደፍራል፤ ሀብትና ንብረትም ይዘርፋል።

ባዩት ነገር በተፈጠረባቸው ድንጋጤ የጤና መታወክ ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ሴቷ መሰለም ከቆቦ ከተማ ተፈናቅለው በደሴ ተጠልለዋል፤  "አሸባሪው የህወሓት ቡድን የፈጸመብን ግፍና በደል ተወርቶ አያልቅም" ሲሉ ነበር ገጠመኛቸውን መግለጽ የጀመሩት ።

"የሽብር ቡድኑ የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር ሆኜ ከሁለት ልጆቼ ጋር ጫካ ለጫካ በእግሬ እንድሰደድ አድርጎኛል፣ ቤት ሰብሮ በመግባት የተቦካ ሊጥ እንኳ ሳይቀር ወስዷል፤ ለመከላከል የሞከሩትንም በጥይት ገድሏል" ሲሉ የቡድኑን ተግባር በምሬት ገልጸዋል።

ወይዘሮ ሴቷ እንዳሉት በአሸባሪው ቡድን ሁለት ጎረቤቶቻቸው በግፍ ተገድለዋል።

በየጫካው የተጎዱ ወጣቶች፣ ደክሟቸው የወደቁ አዛውንቶችና በምጥ የተያዙ ሴቶችን መመልከታቸው ደግሞ አሁን ላይ እንቅልፍ እየነሳቸውና የስነ ልቦና ጫና እንደፈጠረባቸው ነው ።

ወይዘሮ ሴቷ ገጠመኛቸውን በዚሁ አላበቁም፤ "ባለቤቴ  የህወሓት የጥፋት ቡድንን ግፍ ሲመለከት ብር ብሎ እንደወጣ  ነው የተጠፋፋነው፤  እስካሁንም በህይወት ይኑር አይኑር አላውቅም ፤ ብቻ  የተፈጸመው ጭካኔ የቡድኑ አባላት ከሰው የተፈጠሩ አይደሉም የሚያስብል ነው" ሲሉ ነበር የቡድኑን አረመኔያዊነት የገለጹት ።

"አሸባሪው የህወሓት ቡድን አርሶ አደር አይነካም ብለውኝ የግብርና ስራዬን በማከናውንበት ድንገት ይዘውኝ ወደ ማላውቀው አካባቢ ወስደው ወደ ጦርነት ሊማግዱኝ ሲሉ በጫካ አምልጬ ደሴ ከተማ ለመድረስ በቅቻለሁ" ያለው ደግሞ ከአላማጣ ከተማ የመጣው ወጣት ይመር ኑርዬ ነው፡፡

"ድንገት ከገጠመኝ መከራ ለመትረፍ በደመነፍስ ስሮጥ የሽብር ቡድኑ አባላት ሴቶችን ሲደፍሩና ሀብት ንብረት ሲዘርፉ ተመልክቻለሁ" ያለው ወጣቱ ቤተሰቦቹ እስካሁን ድረስ የት እንዳሉ ባለማወቁ በጭንቀት ወስጥ መሆኑን ነው የገለጸው።

ቡድኑ የመላው ኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆኑን ጭካኔ በተመላበት ተግባሩ እያሳየና እያስመሰከረ በመሆኑ ሁሉም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተረባርቦ ሊቀብረው እንደሚገባ ተናግሯል።

ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው ደሴ ከተማ የተጠለሉ ዜጎች ቁጥር ከ60 ሺህ ማለፉን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም