ብሔራዊ የስራ አውደ ርዕዩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተሳታፊዎች ገለፁ

1047

አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2010 የሥራ አውደ ርዕይ ሥራ ፈላጊዎች ሳይጉላሉ በቀላሉ መቀጠር እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች ገለጹ።

የመጀመሪያው ብሔራዊ የስራ አውደ ርዕይ ዛሬ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ተጀምሯል።

በአውደ ርዕዩ ላይ ከተገኙት ተመራቂ ሥራ ፈላጊዎች መካከል ለኢዜአ እንዳሉት አውደ ርዕዩ ከዚህ ቀደም ሥራ ፈላጊዎች ሥራ ለማግኘት የሚደርስባቸውን የጊዜና የገንዘብ ብክነት በመቀነስ በኩል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።

ስለሆነም መሰል አውደ ርዕዮች በስፋት ሊዘወተሩ እንደሚገባ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ አንዳንድ ተቋማት ግን አውደ ርዕዩን ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ብቻ ይጠቀሙበታል ብለዋል።

በምህንድስና የትምህርት መስክ የተመረቀው ወጣት ንጉሴ ተሾመ እንደገለጸው ሥራ ፈላጊዎችን የማይመዘግቡ ነገር ግን ተቋማቸውን ለማስተዋወቅ ብቻ በአውደ ርዕዩ ተካፋዮች ነበሩ።

የአውደ ርዕዩ ጎብኚ ወጣት ሉሊት ተስፋዬ የሥራ ቅጥር የሚያወጡ ተቋማት የሚገኙበትን ቦታና የሥራ ጸባይ ባለማወቅ ተገቢ ያልሆነ ወጪ ለደላላ ትከፍል እንደነበር ተናግራለች።

ወጣት ብርሃኑ አመንቲ በበኩሉ ብዙ ተቋማት የሚገኙት በአዲስ አበባ በመሆናቸው በክልል የሚኖሩ ሥራ ፈላጊዎች ለትራንስፖርት ወጪ መዳረጋቸውን ገልጿል።

ይህ ዓይነት አውደ ርዕይ መዘጋጀቱ በአንድ ቦታ እና በአንድ ጊዜ ለብዙ ተቋማት የቅጥር ጥያቄ ማቅረብ ከማስቻሉም በላይ በአጭር ጊዜ ሥራ የማግኘት ዕድል ከፍተኛ ነው ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀጣሪ ተቋማት በአውደ ርዕዩ ላይ በስፋት አለማሳተፋቸው ሁሉንም ሥራ ፈላጊዎች ሳያካትት መቅረቱን አስተያየት ሰጥተዋል።

እንዲሁም ሥራ ፈላጊዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ልክ ቀጣሪ ተቋማት ባለማሳተፋቸው አንዳንድ ሥራ ፈላጊዎች ሳይመዘገቡ መቅረታቸውን ገልጸዋል።

ወጣት ዊንታና ዳዊት በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የሙያ መስክ በመጀመሪያ ድግሪ ብትመረቅም ከሜድሮክ ውጪ ሌላ አማራጭ አለማግኘቷን ተናግራለች።

ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ የተካሄደው የሥራ አውደ ርዕይ እንደ መጀመሪያነቱ መልካም መሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ የቀጣሪ ተቋማት ቁጥር ግን ወደፊት በሚካሄዱ አውደ ርዕዮች መጨመር እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንደተመለከተው አንዳንድ ተቋማት ያላቸውን የሥራ ዓይነትና የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማስገንዘብ ገለጻ ሲያደርጉ ነበር።

በአውደ ርዕዩ በተሳተፉ ተቋማት ባሉ ክፍት የሥራ መደቦች ላይ ሲያመለክቱ የነበሩ ሥራ ፈላጊዎች በተቋማቱ የመቀጠር ዕድል ካላገኙ መንግስት ባመቻቸው የሥራ ዕድል ተደራጅተው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሥራ አውደ ርዕዩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን 30 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች ቅጥር ይፈጽማሉ ተብሎ ይገመታል።