የሻደይና አሸንድዬን በዓል በአማራ ክልል ደረጃ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

99
ባህር ዳር ነሀሴ 4/2010 የሻደይና አሸንድዬ የልጃ ገረዶች በዓል ባህላዊ ቱፊቱን ለትውልድ ለማስተላለፍ በክልል ደረጃ ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ  አቶ ልዑል ዮሐስ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉን በክልል ደረጃ ከነሐሴ 19 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይከበራል። በዓሉ የሚከበረው የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ በሚያሳይ መልኩ በፓናል ውይይትና በእናቶችና ልጃገረዶች ባህላዊ ጭፈራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዓሉ በክልል ደረጃ ከመከበሩ አስቀድሞ በዋግ ህምራ ሰቆጣ ከተማ የሻደይ፣ በሰሜን ወሎ ላሊበላና ዓይና ቡግና የአሸንድዬና በቆቦ ከተማ ደግሞ የሶለል አሸንድየ በዓል ነሐሴ 16 ቀን 2010 ይከበራል። ቀደም ሲል በክልሉ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎ ይከበር እንደነበርና በሂደት እየተዳከመ መጥቶ በላስታ ላሊበላና በዋግ ህምራ አካባቢዎች ግን ባህላዊ ክንዋኔው በየዓመቱ እየተከበረ ከዚህ መድረሱን ጠቁመዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች በየዓመቱ ማክበራቸውንና ለቱሪዝም አማራጭ መስህብ ማድረጋቸውን ተከትሎ በሌሎች አጎራባች ወረዳዎችና ዞኖች እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል። በዚህ ዓመትም የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች ፌስቲቫልን በክልል ደረጃ በባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን አስተረድተዋል። “ይህም ለዘመናት እየተዳከመ በተወሰኑ አካባቢዎች የነበረው የባህል ትውፊት ለማስፋትና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው'' ብለዋል። በበዓሉ ከየአካባቢው የተውጣጡ እናቶችና ልጃገረዶች የሻደይና አሸንድየ ባህላዊ ጭፈራዎችንና የሚጠቀሙባቸው ባህላዊ ቁሳቁሶችን ለህዝብ እይታ በማቅረብ ልምድ የሚለዋወጡበት ይሆናል። በቀጣይም በዓሉ በስፋት የሚከበርባቸውን አካባቢዎች ለቱሪስት መስህብነት እንዲውሉ የመለየትና የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም አስረድተዋል። በዓሉ ከአራት ዓመት በፊት በሀገር ደረጃ ብሄራዊ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በቀጣይም የአለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ቢሮው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከብሄራዊ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም