የካንሰርና የኩላሊት ንቀለ ተከላ ህክምና መሳሪያዎች ተገዝተው ለህክምና ተቋማት መከፋፈላቸው ተገለጸ

76
አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2010 ከ16 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተገዙ የካንሰርና የኩላሊት ንቀለ ተከላ ህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶችን ለህክምና ተቋማት ማሰራጨቱን የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አስታወቀ። በአገሪቱ በመድኃኒት እና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት እና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት አሁንም ያልተፈታ ችግር እንደሆነ መቀጠሉም ተገልጿል። ኤጀንሲው ባለፈው በጀት እቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የስራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎኮ አብረሃም በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኤጀንሲው በበጀት አመቱ ከ16 ቢሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ  ለጤና ልማት ፕሮግራም የሚውሉ መድሃኒቶችንና የህክምና መሳሪያዎችን ለህክምና ተቋማት አሰራጭቷል ብለዋል። ለካንሰር የጨረር እና ለኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናዎች የሚያገለግሉ መሳሪያዎችና መድሃኒቶች በበጀት ዓመቱ ለተለያዩ ተቋማት ከተሰራጩትመካከል የህከምና መገልገያዎች  ይጠቀሳሉ። ለድርቅና ወረርሽኝ በሽታዎች ተጋላጭ ለሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚያስፈልጉ መድሃኒቶች እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተቋቋሙት የደም ባንኮች አገልግሎት የሚውሉ መድሃኒቶችና መሳሪያዎችም መሰራጨታቸውን ነው ዶክተር ሎኮ የገለፁት። የአገሪቱን የመድኃኒትና ህክምና መገልገያ መሳሪያ ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም የህብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም። ችግሩን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት እንዲቻል ኤጀንሲው ያካሄደውን ጥናት አጠናቆ ወደ ትግበራ መግባቱን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ጥናቱ ከመድኃኒትና መሳሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት፣ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሟላትና የአገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት መጠንን ለማሳደግ  የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ተብሏል።                                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም