በተያዘው በጀት ዓመት የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል አገልግሎት ይቀየራሉ

83

አዲስ አበባ ነሃሴ 11/2013 (ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል አገልግሎቶች የሚቀየሩ መሆኑን የኢኖቬሺንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በ2013 በጀት ዓመት ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ በኤሌክትሮኒክስ ግብይት መከናወኑም ተገልጿል።
የኢኖቬሺንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ ለኢዜአ እንደተናገሩት አገራዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን ወደ ስራ የሚያስገቡ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

ቴክኖሎጂው እንደ አገር የሚተገበር በመሆኑ በአንድ ጊዜ ሁሉም ማህበረሰብ ይጠቀምበታል ተብሎ እንደማይገመትም ጠቅሰዋል፡፡

በግብይት ስርዓቱ ውስጥ የሚያገለግሉ ደረሰኞችን በኦን ላይን ግብይት ውስጥ ህጋዊ የማድረግ ጉዳዮች በአበረታችነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል ዶክተር አብራሃም።

በመሆኑም የዲጂታል ኢኮኖሚ ልውውጡን ህጋዊ የሚያደርጉና ከተለያዩ የመንግስት አሰራሮች ጋር የሚያናብቡ አዋጆችና አሰራሮች ለአቃቤ ህግ መላካቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት አዲሱ ፓርላማ ስራ እንደጀመረ ፀድቆ ቁልፍ የሚባሉ የመንግስት አገልግሎቶች የዲጂታል ኢኮኖሚውን ይቀላቀላሉ ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የዲጂታል ትራንስፖርቴሺን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀኔራል ዶክተር አብዮት ባዩ፤ አሁን ላይ በርካቶች የዲጂታል ኢኮኖሚውን እየተቀላቀሉ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማስጀመርና ለማስፋፋት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱን ለማህበረሰቡ የማስተዋወቅ ስራው በከፍተኛ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎታቸውን ወደ ዲጂታል በመቀየርና ተገልጋዮቻቸውን በዘርፉ በማስተናገድ ቀዳሚ መሆናቸውን ጠቅሰው ሌሎች ተቋማትም ይህንን አርአያ እንዲከተሉ መክረዋል።

በ2013 ዓ.ም ብቻ ከ300 ቢለዮን ብር በላይ በኦን ላይን የግብይት ስርዓት መዘዋወሩን የጠቀሱት ዶክተር አብዮት ይህም በዘርፉ ያለውን መነቃቃት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አያልነህ ለማ በበኩላቸው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን ተከትሎ የኦን ላይን ግብይት መጀመሩ ጊዜና ገንዘብን ከመቆጠብ አልፎ ዝርፊያና ስርቆት የመሳሰሉ ወንጀሎችን ለመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ በርካታ ችግሮችን እንደሚፈታና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ በርካታ የህግ ጥሰቶችን ለመቆጣጠር ይረዳል ብለዋል።

የዲጂታል ግብይት ስርዓቱ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመቀመር በሚስጥርና በጥንቃቄ የሚከወን መሆኑንም ገልጸዋል።

በዲጅታል ግብይት አጠቃቀም በደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ ከፍተኛ እድገት እያሳየ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዓለም ላይ ድጅታል ግብይትን በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ስዊዘርላንድ፣ ጀርመን እና ሆላንድ ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም