በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተከስቶ የነበረው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እየተቃለለ ነው

115
አዲስ አበባ ነሃሴ 4/2010 በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተከስቶ የነበረው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እየተቃለለ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። በአገር አቀፍ ደረጃ የስኳር መድኃኒትን ጨምሮ በርካታ መድኃኒቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ ህሙማን ለችግር ሲዳረጉ ቆይተዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከስቶ የነበረው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እየተቃለለ ነው። መንግስት ይህንን ችግር ለማቃለለ በአሁኑ ወቅት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ውጤታማ እንደሆኑ የገለጹት ሚኒስትሩ በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ተጋርጦ የነበረውን ችግር ለመፍታት ከውጭ ለሚገቡ መድኃኒቶች ቅድሚያ እንደተሰጠ ተናግረዋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ከውጭ በሚገቡ ማንኛውም ዕቃዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበረ የተናገሩት ዶክተር አሚር በአገር አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት አቅርቦቱ በቂ እንዳይሆን ትልቁን ድርሻ እንደወሰደም አስረድተዋል። በተለይ በስኳር ህመም መድኃኒት ላይ አጋጥሞ የነበረው የአቅርቦት እጥረት መድኃኒቱን የሚያመርተው ድርጅት ካደረገው የስያሜ ለውጥ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት በኀብረተሰቡ ዘንድ ውዠንብር ተፈጥሮ እንደነበረም አስረድተዋል። በኀብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረውን ውዥንብር ለማስወገድ ለባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል። በአጠቃላይ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት እና ከስኳር መድኃኒት ስያሜ ጋር ተያይዞ የነበረው የአቅርቦት ችግር በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ የተወገደ መሆኑን ዶክተር አሚር አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም