የባህል ህክምና በምርምር ባለመታገዙ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ጥቅም ማግኘት አለመቻሉ ተገለጸ

262
አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2010 በኢትዮጵያ የባህል ህክምና በሳይንሳዊ ምርምር አለመታገዙ ከዘርፉ የሚጠበቀው ያህል ጥቅም እንዳይገኝ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ባህል ማዕከል "የኢትዮጵያ ባህላዊ መድሃኒቶች ከየት ወዴት" በሚል ከሚመለከታቸው ጋር ዛሬ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ የባህል ህክምና ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የመንግስት ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል። የአስር አመት ልጅ እያሉ ጀምሮ የባህላዊ ህክምና መስጠት የጀመሩት አሁን ሃምሳዎቹን ያለፉት መምህር መኳንንት ብርሃኑ ሙያውን ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት እንደሆነ ይገልጻሉ። ከ30 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የባህል መድሃኒቶችን እንደሚሰጡ የሚናገሩት መምህር መኳንንት እስከ 8ኛ ክፍል መደበኛ ትምህርት ከመከታተላቸው ውጪ ከሙያቸው ጋር የሚዛመድ ስልጠናም ሆነ ትምህርት አለመውሰዳቸውን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከእንስሳት፣ እጽዋትና ማእድናት የሚገኙ የተለያዩ መድሃኒቶች መገኛ መሆኗን በስራ ቆይታቸው መታዘብ ችለዋል። ነገር ግን የባህል ህክምናውና ከዘመናዊ ህክምና ተቀራርበው አለመስራታቸው የባህል መድሃኒቶችን በምርምር ማገዝ ባለመቻሉ በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ያምናሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማኮግኖሲና ፋርማሲቲካል ኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ቢኒያም ጳውሎስ "የኢትዮጵያ ባህላዊ መድሃኒቶች ከየት ወዴት" በሚል ባቀረቡት ጹህፍ ባህላዊ ህክምና በምርምር እየታገዘ አለመሆኑን አመላክተዋል። በኢትዮጵያ 80 በመቶ የህብረተሰብ ክፍል ለበሽታ መከላከል፣ ለፈውስ እንዲሁም ለቀዶ ጥገና የባህላዊ መድሃኒቶች እንደሚጠቀም በጹሁፋቸው አስቀምጠዋል። ህክምናው ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ህክምናውን ከዘመናዊ ህክምና ጋር አጣጥሞ ለማስኬድ አልተቻለም። እንደ ጹሁፍ አቅራቢው ገለጻ የባህል መድሃኒቶች ህክምናውን በሚሰጡት ባለሙያዎች ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ ነው ቢባልም በሳይንሳዊ መንገድ የተሰጠው ማረጋገጫ የለም። በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ ለመድሃኒት የሚውሉ የተለያዩ እጽዋት መገኛ አገር ብትሆንም በሚፈለገው መልኩ መጠቀም አልቻለችም የሚል መደምደሚያ አላቸው። በባህላዊ እና ዘመናዊ ህክምና መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ አለመሆን፣ ባህላዊ መድሃኒቶችን ለማሳደግ የሚደረጉ ጥናቶች አነስተኛ መሆን፣ ባህላዊ መድሃኒቶችን አሰባስቦ የሚይዝና ጥበቃ የሚያደርግ አካል አለመኖር፣ ለእጽዋቶች የሚደረገው ጥበቃ አነስተኛ መሆን ተጨማሪ ችግሮች ናቸው ብለዋል። ባለቤት እንዲኖረው ማድረግ፣ በባህል ህክምና ለተሰማሩ ሙያተኞች ስልጠና መስጠት፣ ፈዋሽነታቸውን ማረጋገጥ፣ የባህል ህክምና በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ ማድረግ በመፍትሄነት አስቀምጠዋል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጌታቸው ጣላቸው እንዳሉት፤ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር ባህላዊ መድሃኒቶች ላይ ጥናት እየተደረገ ነው። ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆንም የባህል መድሃኒቶች በፖሊሲ እንዲካተቱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከእጽዋት መጥፋት ጋር በተገናኘም የብዝሐህይወት ኢንስቲትዩት ከ800 በላይ እጽዋቶችን ከመጥፋት መታደጉን ገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም