የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻድ አቻውን 49 በመቶ ድርሻ ሊገዛ ነው

185
አዲስ አበባ ነሃሴ 4/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአወሮፓዊያን አቆጣጠር በመጪው ጥቅምት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን አዲሱ የቻድ አየር መንገድን የ49 በመቶ ድርሻ ሊይዝ እንደሆነ ተገለፀ። አዲስ የተቋቋመው የቻድ አየር መንገድ 51 በመቶ የባለቤትነት ድርሻን የቻድ መንግስት የሚይዝ ሲሆን ከአትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በሽርክና ለመስራት ውይይት እየተካሄደ መሆኑም ተመልክቷል። መቀመጫው በኬንያ የሆነው 'ዘ ኢስት አፍሪካ ' እንደዘገበው በሁለቱ አየር መንገዶች መካከል ተግባራዊ በሚሆነው የጋራ ትብብር መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው አፍሪካ ለሚሰጠው የበረራ አገልግሎት የቻድ አየር መንገድን ማዕከል አድርጎ ይሰራል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቻድ በተጨማሪ የጅቡቲን፣ የኢኳቶሪያል ጊኒን እና የጊኒን አየር መንገዶች በሽርክና ለመያዝ ከአየር መንገዶቹ ጋር እየተነጋገረ መሆኑም ተገልጿል። ከዚህ በፊት አየር መንገዱ የቶጎ አየር መንገድን 40 በመቶ፤ የማላዊ አየር መንገድን ደግሞ 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ይዞ በሽርክና እየሰራ ይገኛል። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተዘግቶ የቆየውንና በዚህ ዓመት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን የዛምቢያን አየር መንገድ 45 በመቶ ድርሻ ባለፈው ጥቅምት ወር መግዛቱም ተመልክቷል። በገቢና በትርፋማነቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣይም የሞዛንቢክ አየር መንገድን ሙሉ ባለቤትነት በመያዝ  ለማስተዳደር እቅድ እንዳለውም ተገልጿል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም