የአዲስ አበባ ከተማ የአመራር ለውጥ በክፍለ ከተሞችና በወረዳዎችም ይካሄዳል-ኢንጅነር ታከለ ኡማ

954

ነሃሴ 4/2010 በመዲናዋ እየተከናወነ ያለው የአመራር ለውጥ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃም እንደሚካሄድ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናገሩ ።

ምክትል ከንቲባው ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አዳዲስ የካቢኔ አባላትን ሹመት ባጸደቀበት ወቅት ነው።

ዛሬ የተሾሙት የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት መመዘኛ ኢትዮጵያዊነታቸው፣ ብቃታቸውና የትምህርት ዝግጅታቸው መሆኑንም ኢንጅነር ታከለ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ትንሿን ኢትዮጵያ የምትወክልና የአፍሪካ መዲና በመሆኗ ከተማዋን የሚመጥን እና የነዋሪዎቿን ጥያቄ የሚመልስ ስራ መስራት ከአዲስ የካቢኔ አባላት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው የአመራር ሹመቱ ብቁ ወጣቶችን እና ሴቶችን ያካተተ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በቀጣይም በማዘጋጃ ቤታዊ የአገልግሎት ዘርፍ መስሪያ ቤቶች የአመራር ሹም ሽር ከምክር ቤትና ከምክር ቤት ውጭ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላት በተሾሙት አዲስ የካቢኔ አበላት ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አቅርበው ያሾሟቸው የካቢኔ አባላት ወጣትና ለተመደቡበት የስራ ዘርፍ የሚመጥኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአዲሱ ካቢኔም የሴት አመራሮች ቁጥር የተሻለ በመሆኑ የአመራር ለውጡ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

አዲሱ አመራር የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚያነሳቸውን በርካታ ችግሮች እና ቅሬታዎች ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው የገለጹት።

የምክር ቤት አባላቱም ለነባር የካቢኔ አባላት አመራሮች በቆይታ ዘመናቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ አምስግነዋል።

አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ተወላጅ የሆኑ የካቢኔ አባላት መሾማቸውም አዲስ አበባ በአዲስ አበባ ልጆች ትመራ የሚለውን በአንጻራዊነት ሊመልስ የሚችል እንደሆነም ነው ያነሱት።

አዲሶቹ የአመራር አባላት በቀጣይ ስራቸው ላይ ስኬታማ እንዲሆኑም የበኩላችንን ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል ብለዋል።