በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት ወረርሽኝ መሆኑ እንደቀጠለ ነው

237
አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2010 ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ በሽታ ጉዳይ እየተረሳና  ትኩረት እየተነፈገው መሆኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ይነገራል። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ደግሞ የቫይረሱ ስርጭት ከ1 በመቶ በላይ ከሆነ በአንድ አገር ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ወረርሸ መከሰቱን ያሳያል። በኢትዮጵያ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በየጊዜው በተከናወኑ የዘመቻ ሥራዎች የስርጭት መጠኑ ከነበረበት ወደ 1 ነጥብ 2 በመቶ ዝቅ ማድረግ ቢቻልም አንድ አገር ከወረርሽኝ ነፃ ነች የሚባለው የሥርጭት መጠኑ ከአንድ በመቶ በታች ሲሆን ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት የሥርጭት መጠኑን ከአንድ በመቶ በታች ለማውረድ እ.ኤ.አ. በ2030 ደግሞ አንድም ሰው ኤች አይ ቪ እንዳይጠቃ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ የሥርጭት መጠኑን ለጊዜው ማለዘብ መቻሉ ግን በኤች አይ ቪ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ፊታቸውን ወደ ሌሎች ጉዳዮች እንዲያዞሩ ማኅበረሰቡም እንዲዘናጋ እድል ፈጥሯል፡፡ ከፌደራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ በ2009 ዓ.ም ብቻ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ27ሺህ በላይ መሆኑን የጠቆመ ሲሆን የስርጭት መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የቫይረሱ ስርጭት በተለይ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በሚካሄዱባቸው ቦታዎች፣ አዲስ በሚመሰረቱ ከተሞች እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ ነው ተብሏል። በአዲስ አበባ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ምን እየተሰራ ነው? ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቶች ስለዚህ ጉዳይ ምን ያህል ያውቃሉ? የሚለውን ሐሳብ ለመዳሰስ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረን አስተያየቶችን ሰብስበናል። በጉዳዩ ዙሪያ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሰባት ጊዜያዊ ነጻ የምርመራ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው የመመርመሪያ ቦታዎች ውስጥ በመገናኛና በአውቶቢስ ተራ ተገኝተን በስፍራው አገልግሎት እያገኙ የነበሩትን አነጋግረናል። መገናኛ በሚገኘው የነጻ መመርመሪያ ስፍራ ምርመራ ሲያደርግ የነበረው ወጣት ግሩም ተፈራ ስለ ሻይረሱ ስርጭት ጥሩ ግንዛቤ እንዳለው ይናገራል። ወጣቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቂ ግንዛቤ ኖሮት እራሱንና ቤተሰቡን ከቫይረሱ ሊጠብቅ እንሚገባ ገልጾ በተለይ ወጣቱ ጥንቁቅ መሆን አለበት ይላል። ''በሚዲያው በኩል የሚደረገው ቅስቀሳ ከበፊቱ ቀዝቀዝ ያለ ስለሆነ ወጣቱ ተመርምሮ እራሱን ማወቁ ትንሽ ቀነስ ያለ ይመስለኛል፤ ቢሆንም ወጣቱ የለውጥ ሀይል አንቀሳቃሸ እንደመሆኑ መጠን እራሱን አውቆ ጤንነቱን ጠብቆ ወደ እድገት ጎዳና በምናደርገው እንቅሰቃሴ ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ቢያደርግ ደስ ይለኛል'' ብሏል፡፡ ሌላዋ በአውቶቢስ ተራ በሚገኘው የመመርመሪያ ስፍራ የደም ምርመራ ሲያደርጉ ያገኘናቸው ወይዘሪት ሃሊማ መሃመድና ወጣት መስታወት ዘርይሁን በየጊዜው ምርመራ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። ቫይረሱ ልክ እንደጠፋ ተደርጎ የሚታሰብ ቢሆንም ስርጭቱ እየጨመረ ነው የሚል ዕምነት እንዳላቸው ገልጸው በተለይ ወጣቱ እራሱን ከቫይረሱ ጠብቆ ሊኖር ይገባል ብለዋል። ወይዘሪት ሃሊማ መሃመድ እንዳለችው '' በየሶስት ወሩ እየተመረመርኩ  እራሴን አውቃለሁኝ  ፤በተለይም ለወጣቱ ማስተላለፍ የምፈለገውም መልዕክት ቢኖር በየሶስት ወሩ እየተመረመሩ እራሳቸውን እንዲያውቁ እመክራለሁኝ።” “እዚህ የመጣሁት ተመርምሬ እራሴን ለማወቅ ነው። ከዚሀ በፊት ተመረምሬ እራሴን አወቄ ነጻ ነኝ አራት ወር ይሆነኛል ከተመረመርኩኝ አሁን ድጋሚ ለመታየት ነው የመጣሁት በፈቃደኝነት ፣እዚህ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ በነጻ ነው የምናገኘው''ያለችው ደግሞ ወጣት መስታወት ዘርይሁን ነች፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙት ሰባቱ የጊዜያዊ የመመርመሪያ ስፍራዎች መካከል በሁለቱ ላይ ያደረግነውን ቅኝት ይዘን ወደ ፌዴራል ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽህፈት ቤት አቅንተን ነበር። በጽህፈት ቤቱ የዘርፈ ብዙ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ክፍሌ ምትኩ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ጉዳይ  በአሁኑ ወቅት የተረሳ ያህል ዝም ተብሏል፣ ለዚህም እንደምክንያት ተብሎ ከሚነሱት ውስጥ አንዱ የመዘናጋት አዝማሚያ መፈጠሩ ነው ይላሉ። ዳይሬከተሩ የወጣቶች ተጋላጭነትም ከጊዜ  ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረው ለዚህም አንዱ ምክንያት በቂ መረጃ ባለማግኘት ነው ብለዋል። ''ቅርብ ጊዜ የወጡት ጥናቶች እንደሚያሳዩት እድሜያቸው  ከ15 እስከ 24 ያሉ ወጣቶች ኤች አይቪ ኤድስን የመከላከል አጠቃላይ እውቀት አላቸው ተብሎ የሚታሰበው በወንዶች 39 በመቶ ነው በሴቶች ደግሞ 24 በመቶ ነው ይህ ማለት ከዚህ ውጭ ያለው በመቶኛ የሚሰላ ቁጥር ኤች አይቪ ኤድስን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል እውቀት የላቸውም።'' በተጨማሪም  መጤ ባህል በመከተል የምሽት ቤቶች መብዛትና የሺሻ ቤቶች በከተማዋ መብዛት ለቫይረሱ መስፋፋት እንደ አንዱ ምክንያት የሚቆጠር መሆኑን ዳይሬክተሩ አክለዋል። አሁን ባለው መረጃ መሰረትም በአዲስ አበባ የስርጭት ምጣኔው 3 ነጥብ 4 በመቶ  በመሆኑ ስርጭቱን የመከላከል ጉዳይ የአንድ አካል ጉዳይ ብቻ ባለመሆኑ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራውን ለማከናወን ሁሉም ያገባዋል ብለዋል። አሁን እየተስተዋለ ላለው የኤች አይ ቪ ግርሻ ከመሰረቱ ለመፍታት ምን መደረግ እንዳለበት በተለይ ወጣቱን በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል። ''ልጆች በራሳቸው አቅም እራሳቸውን መምራት እንዲችሉ የህይወት ክህሎት ስልጠናዎች ማግኘት መቻል አለባቸው እንግዲህ ይህ ሲባል ከቤተሰቦቻቸው ጀምሮ ከትምህርት ቤቶቻቸው ጀምሮ ሁኔታዎች ሁሉ ምቹ መሆን አለባቸው ለተማሪዎች የሰብዕና መገንቢያ የሆኑ ነገሮች ስራዎች ሁሉ መሰራት አለባቸው ።'' የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርት እ.ኤ.አ. እስከ 2021 አሁን ያላው የቫይረሱ ስርጭት በዚሁ ከቀጠለ  ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር ወደ 754 ሺህ 256 እንደሚያሻቅብ አስቀምጧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም