ደቡብ ሱዳን ከሦስት ዓመታት በኋላ ምርጫ ልታካሂድ ነው

75
አዲስ አበባ ነሃሴ 4/2010 ደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነቷን ለመቋጨት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ገለጹ። አገሪቱ ከሦስት ዓመታት በኋላ ብሔራዊ ምርጫ እንደምታካሂድም በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ጉዳዮ ላይ ዛሬ መግለጫ የሰጡት አምባሳደሩ አስታውቀዋል። አምባሳደሩ እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረው የደቡብ ሱዳን የሠላም ድርድር በሦስተኛ ወገኖች ፍላጎት ሳቢያ በተለያየ ጊዜ ሲደናቀፍ ቆይቷል። ድርድሩን ሲመራው የነበረው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን በውጭ ኃይሎች ጫና ተደርጎበት እንደነበርም ነው አምባሳደሩ ያመለከቱት። ያም ብቻ ሳይሆን አካባቢው ጭምር በሌሎች ኃይል መዳፍ ሥር መቆየቱን ጠቅሰው በዚህም በደቡብ ሱዳን አላስፈላጊ በሆነ መንገድ በአገሪቱ የሚፋለሙት ሁለቱ ኃይሎች ጦር እንዲሰማራ መደረጉን አስታውሰዋል። ይህም ለበርካታ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ህልፈተ ህይወት፣ ለኃብትና ንብረት መውደም  ምክንያት መሆኑን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ተናግረዋል። ይሁንና በቅርቡ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ቡድኖች በሱዳን ካርቱም የደረሱበት ስምምነት ይህንን ሁኔታ በመቀየር በአገሪቱ ሠላም እንዲሰፍን አስችሏል ብለዋል። "በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ምንም አይነት የጥይት ድምጽ አይሰማም" ያሉት አምባሳደሩ ይህም እውን ሊሆን የቻለው ኢትዮጵያን ጨምሮ የጎረቤት አገራት ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት እንደሆነ ጠቅሰዋል። በተለይም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በዚህ ረገድ ላደረጉት አስተዋጽዖ አምባሳደሩ ምስጋና አቅርበዋል። "አሁን ባለው ሁኔታ መጪውን ስምንት ወራት ቡድኖቹን ማደራጀት ይጠይቃል፤ ካዛም በኋላ ለ30 ወራት ማዕከላዊ መንግሥትን የማጠናከር ሥራ ይሰራል" ብለዋል። ይህንንም ተከትሎ ከሦስት ዓመታት በኋላ ምርጫ ይካሄዳል። በደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በተቀሰቀሰው ግጭት በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለህልፈተ ህይወት ሲዳረጉ፤ አያሌዎች ደግሞ ቆስለዋል። ከሁለት ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናዊያን የእርስ በእርሰ ጦርነቱን ሸሽተው ሲሰደዱ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በአገራቸው ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው የነበሩት የቀድሞው ምክትላቸው ዶክተር ሬከ ማቻር በአገሪቱ የሚካሄደው ግጭት አንዲያበቃ የሚያስችል የሰላም ስምምነት የፈረሙት ባለፈው ሳምንት በሱዳን መዲና ካርቱም ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤትን እና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል የተደረሰውን ስምምነት አድንቀዋል። በቁርጠኝነት ተግባር ላይ ያውሉት ዘንድም አሳስበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም