የኦነግ እና የመንግስት ስምምነት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚያመች በጎባ ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ

46
ጎባ/ጊምቢ ነሀሴ 4/2010 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና መንግስት የደረሱበት ስምምነት ሰላማዊ እንቅስቃሴን በማረጋገጥ ልማትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር በጎባ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች የተገኘውን ሰላም አስጠብቀው የአካባቢያቸውን ልማት ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ  ተናግረዋል። ከጎባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መስፍን ከበደ እንዳሉት በውጭ ይንቀሳቀሱ  የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ መንግስት ጥሪ ማድረጉ ከኦነግ ጋር ለተፈጸመው ስምምነት መደላደል ፈጥሯል፡፡ ጥሪውን በመቀበል ቀደም ሲል የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላም ለመታገል ወደ ሀገር እንደገቡ የጠቀሱት አቶ መስፍን በስምምነቱ መሠረት ኦነግም ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑ በየደረጃው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ የሰላም ስምምነቱ በአካባቢያቸው ብሎም በክልሉና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለጹት ደግሞ በከተማው የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት አቶ ተሾመ አሰፋ ናቸው፡፡ በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነታቸውን በማጥበብ አንድ በሚያደርጋቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ እንዲሰሩ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመልክተዋል፡፡ በከተማዋ በንግድ ሰራ የተሰማሩ አቶ ሁሴን ኢብራሂም   በበኩላቸው" ስምምነቱ በሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በሰላማዊ መልኩ እንዲታገሉ በተሰራው ስራ የመጣ ውጤት ነው" ብለዋል፡፡ ድርጅቶቹ ጊዜ ያለፈበትን የትጥቅ ትግል በመተው ወቅቱ ከደረሰበት የአስተሳሰብ ሂደት ጋር የሚሄድ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል እንዲያካሄዱ ፍላጎታቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ስምምነቱ የጸጥታ ስጋት እንዳይኖር ሰላማዊ እንቅስቃሴና ልማትን  ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ያመለከቱት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተገኘውን ሰላም አስጠብቀው የየአካባቢያቸውን ልማት ለማስቀጠል ድርሻቸውን እንደሚወጡ የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ የከተማው የሀገር ሽማግሌ አቶ ኃይሌ ሪቂቱ በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱም ሆነ በአካባቢያቸው ለውጥ እንዲመጣ የወጣቱ ትግል ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በከተማቸውና አካባቢው ሰላምና መረጋጋት በመታየቱ ይህን   ምቹ ሁኔታ በማስቀጠል ልማትን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ  አመልክተዋል። የጊምቢ ከተማ አባ ገዳ ተሊላ ቦጃ በበኩላቸው "የሚመካከር ሰው ሁሌም የተሻለ ስራን ስለሚሰራ በመደማመጥና በመነጋገር የተገኘውን ሰላም በልማቱም በመድገም ሁሉም መረባረብ አለበት" ብለዋል። አስተያየት ሰጪው እንዳሉት በየደረጃው ያሉ አመራሮች የለውጥ ሀዋሪያ በመሆን ህብረተሰቡን ማንቃትና ወደ ላቀ የእድገት ጎዳና መምራት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር እጦትና የመሰረተ ልማት በአግባቡ አለመሟላት የህዝቡን ቁጣ በማንኛውም ሰዓት ሊቀሰቅስ ስለሚችል ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርበው በመወያየት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ኦነግና መንግስት ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህም የአካባቢው ሰላምና መረጋጋት በመጠናከሩ ይህንኑ አስጠብቀው ልማት ለማስቀጠል እንደሚጥሩ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። በውጭ ሀገራት የሚንቀሰቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው መጥተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ቀደም ሲል የኦሮሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር መግባታቸው ይታወቃል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም