በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የተገነቡ አምስት የንፁህ መጠጥ ውሃ ኘሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

62
ነቀምቴ ነሀሴ 4/2010 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ37 ነጥብ 7 ሚሊዮን  ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጅ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብደና ያደሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በቅርቡ ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት አምስት መካከለኛና ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ናቸው። ሆሮ ሻምቡ ከተማን ጨምሮ. ጮማን ጉዱሩ፣ አቤ ዶንጎሮ፣.አባቦ ጉዱሩ እና ጅማ ገነቲ ወረዳዎች ውስጥ የተገነቡት የውሃ ተቋማት  ከ152 ሺህ በላይ የአከባቢውን ነዋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በመንግስትና በሕዝብ የገንዘብ፣ የጉልበትና የቁሳቁስ ተሳትፎ መከናወኑንም ተናግረዋል። ኃላፊው እንዳሉት የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በኮንትራክተሮች አቅም ማነስና በሌሎችም ምክንያቶች ለስድስት ዓመታት በመጋተቱ ህብረተሰቡ ቅሬታውን ሲያነሳ እንደነበር ገልጸው በዚህ ዓመት በልዩ ትኩረት በተደረገው ርብርብ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን አውስተዋል። የውሃ ፕሮጀክቶቹ መሰራት የዞኑን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከ59 በመቶ ወደ 65 በመቶ ማሳደጉን ገልጸዋል። የጅማ ገነቲ ወረዳ የዳዱ 01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ አዱኛ ታርኩ አካባቢያቸው በቂ የውሃ አገልግሎት ባለመኖሩ በተለይ በበጋ ወቅት ለከፍተኛ ችግር እንደሚጋለጡ ተናግረዋል፡፡ በአከባቢያቸው አዲስ የተሰራው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ የሳቸውንና የአከባቢውን ነዋሪ ችግር በዘላቂነት መቅረፉን ተናግረዋል። የአባቦ ጉዱሩ ወረዳ የሞቲ ቃዩ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሃብቴ ተክሉ በበኩላቸው ከአሁን በፊት የምንጭ ውሃን በወረፋ እየቀዱ ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው  አሁን  ግን በአቅራቢያቸው የውሃ  ማከፋፈያ ቦኖ በመገንባቱ ችግራቸው መቃለሉን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም