በሃገሪቱ እየመጣ ላለው ለውጥ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው…አቶ ጃዋር መሀመድ

4495

ባህር ዳር ነሐሴ 3/2010 በኢትዮጵያ እየታየ ላለው ለውጥ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ከፍተኛ ሚና መጫዎታቸውን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሃመድ ገለጹ።

በአቶ ጃዋር የሚመራ ቡድን ዛሬ ማምሻውን ባህርዳር ከተማ ሲገባ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል፡፡

ወደ ክልሉ የመጡትም የአማራና ኦሮሞ ህዝቦችን “ተፈጥሯዊ ትስስር ለማጠናከር” እና የክልሉ ህዝብና መንግሥት ለለውጡ እውን መሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ለማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ክልል ህዝቦች ተፈጥሯዊ ቁርኝት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ በታሪክም የማይነጣጠሉ፣ ሊነጣጠሉም የማይችሉና የማይገባቸው ዘላቂ ግንኙነት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለዘመናት የዘለቀውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግም በምሁራን፣ በአመራሩና በህዝቡ ዘንድ ሰፊ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ለውጡን ያመጣው የአብሮነት ሂደት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ እርሳቸውም እገዛ እንደሚያደርጉ ነው አቶ ጃዋር ያረጋገጡት።


በሃገሪቱ የመጣው የተስፋ ጭላንጭል የበለጠ እንዲታይ የሁለቱ ክልል ህዝቦች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የሁለቱ ክልል ህዝቦች በሰላም አብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን የላቀ ትብብር ማምጣት ለሃገሪቱ አንድነት፣ ለዴሞክራሲና ሰላም ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው፤ በቆይታቸውም ይህንን የሚያጠናክር ውይይት ይደረጋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው በአቶ ጃዋር መሃመድ የሚመራው የልኡካን ቡድን ወደ ባህር ዳር በመምጣቱ በክልሉ ህዝብ ስም አመስግነዋል።

“በቆይታቸውም ወደፊት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር በሚረዱ ተግባራት ላይ ውይይት ይደረጋል” ብለዋል።