ስምምነቱ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስተያያት ሰጪዎች ተናገሩ

63
መቱ/አምቦ/ ነቀምቴ ነሓሴ 3/2010 ኦነግ እና መንግስት የደረሱበት ስምምነት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመቱ፣ አምቦና ነቀምቴ ከተሞች አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ስምምነቱ ሰላምን በማረጋገጥ ለሀገርና እድገት በጋራ ለመሰማራት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በመቱ የሚኖሩት  የመንግስት ሰራተኛ አቶ ተፈሪ አለማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከኤርትራ መንግስት፣  ኦነግና ግንቦት ሰባት ጋር ሰላም እንዲወርድ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ተናግረዋል። እንደ  አቶ ተፈሪ ገለጻ በተለይ ለረጅም ዓመታት የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ ወስዶ የቆየው ኦነግ በሰላማዊ ትግል ለመሳተፍ መስማማቱ ለክልሉና ለሀገር እድገት የሚበጅ ነው፡፡ በከተማው በእህል ንግድ ስራ የተሰማራው ወጣት ገመቺስ አያና በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ልዩነትን በውይይት መፍታት የሚያስችል መድረክ በመፈጠሩ ሌሎች ያኮረፉ አካላትም በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲቀሳቀሱ የሚጋብዝ መሆኑን ተናግሯል። መንግስትና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት በክልሉና ሀገሪቱ የጸጥታ ስጋት እንዳይኖር በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡ የትጥቅ ትግል ፋሽኑ ያለፈበት በመሆኑ ሁሉም በሰላማዊ ትግል እንዲሳተፍ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያቀረቡት ጥሪ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በከተማው ቀበሌ አንድ በቡና ንግድ የተሰማሩት ወይዘሮ ጫልቱ ሀሰን ናቸው። በተመሳሳይ በአምቦ ከተማ የዜሮ ሁለት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደራራ ተርፋሳ እንደገለጹት ኦነግ ለረጅም ጊዜ በውጪ ሀገራት ሲያካሄድ የቆየውን ትግል ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ መወሰኑ የሚበረታታ ነው። ሌላው በከተማዋ የቀበሌ አንድ ነዋሪ አቶ ጉተማ ኪታ ለዘላቂ ሰላም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል። ኦነግ ለበርካታ ዓመታት ለክልሉ ህዝብ ጥቅም መከበር ሲሰራ የቆየ አንጋፋ ድርጅት መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ከመንግስት ጋር የደረሰበት ስምምነት ደግሞ ለህዝቦች አንድነትና  ለሀገር ዕድገት እንዲሰራ የሚበጅ መሆኑን አመልክተዋል። በሌላ በኩል የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው  አቶ ማሞ ኪትላ በሰጡት አስተያየት ኦነግ ከመንግስት ጋር የደረሰበት ስምምነት ችግሮች ተቀራርቦ በመፍታት ለዘላቂ ስላምና አንድነት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ "ህብረተሰቡም የዴሞኪራሲ መብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም የሚያግዝ ነው" ብለዋል። አቶ ለሜሳ ረጋሳ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ያለው የአንድነት እንቅስቃሴ ለክልሉና ለአጎራባች አካባቢዎች የሚጠቅም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "በመንግስትና በኦነግ  መካከል የተደረገው ስምምነት በውጭ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሀገሪቱ ልማት ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ በር ከፋች ነው" ብለዋል። ስምምነቱ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላም፣ ዴሞክራሲና አንድነት መስፈን አስፈላጊ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ሌላው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው ወጣት ገመቺስ ዋቅጅራ ነው፡፡ መንግስትና ኦነግ ያደረጉት ስምምነት መቻቻልን፣አብሮነትን፣መደጋገፍ፣አንድነትንና በጋራ የማልማት አመለካከቶችን አጎልብቶ ለተሻለ ለውጥና እድገት እንደሚጠቅም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በውጭ የሚንቀሰቀሱ የፖለቲካ ድረጅቶች ወደ ሀገራቸው መጥተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ መንግስት ባቀረበው ጥሪ መሰረት የተለያዩ ፓርቲዎች ወደ ሀገር መግባታቸው ይታወቃል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም