በሰሜን ሸዋ የበጎ አደርጎት ድርጅቶችና ማህበራት የልማት አጋር በመሆን ድጋፍ እየሰጡ ናቸው

50
ደብረብርሃን ነሀሴ 3/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚንቀሳቀሱ የበጎ አደርጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለአካባቢው  የልማት አጋር በመሆን ድጋፍ የሰጡ መሆናቸው ተገለጸ፡፡ በዞኑ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ማህበራት በስራዎቻቸው ዙሪያ ከአካባቢው የመንግስት አካላት ጋር በጫጫ ከተማ ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት የዞኑ ገንዘብና ኢኮኖሚ መምሪያ የመንግስት ትብብር ባለሙያ አቶ ጌቱ መንግስት እንዳሉት ድርጅቶቹና ማህበራቱ በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት ለ92 ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል 186 ሚሊዮን ብር መድበው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ ከአካባቢው የመንግስት አካላት ጋር ተፈራርመው ወደ ስራ የገቡት እነዚህ  48 ድርጅቶችና ማህበራት እስካሁን 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ  ስራ ላይ በማዋል ለአካባቢው ህብረተሰብ የልማት አጋር በመሆን ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ የትምህርት ቤት ማስፋፋትና የውስጥ ድርጅት ማሟላት ፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ጤና ኬላዎች ግንባታና በቁሳቁስ ማደራጀት ፣ የባለሙያዎች አቅም ግንባታ ፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ ሴቶችና ህጻናት መደገፍ በአካባቢው ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ይገኙበታል። ሆኖም በስራው ሂደት የግልጸኝነት መጓደል፣ አሳማኝ ሪፖርት ያለማቀረብ፣ ከመንግስት ጋር በተዋዋሉት መሰረት ፈጽሞ ያለመገኘትና የስራዎች ማጓተት በመስተዋሉ  ይህ ችግር እንዲፈታ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚያስፈለግ ባለሙያው ጠቁመዋል። ተስፋ ብርሃን ህጻናትና ቤተሰብ ልማት ደርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተረፈ ሲሳይ  በበኩላቸው  ድርጅታቸው ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ  በጤና፣ በትምህርት፣ በሴቶችና ህጻናት ድጋፍ ላይ እየሰራ  እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ እስካሁንም ባሶና ወራና፣ ደብረብርንሃን ከተማና አጎራባች ወረዳዎች  ህብረተሰቡን   ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎችን ማከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡ በቀወት ወረዳና  አካባቢው  ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ  በትምህር ቤት ማጠናከርና  ቁሳቁስ አቅርቦት እንዲሁም   በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በፕላን ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኦፊሰር ሼህ ኢድሪስ ሲራጅ ናቸው፡፡ ስራቸውን በአግባቡ ለማቀላጠፍ  በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት ሊደግፏቸውና ሊከታተላችው እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። በውይይት ወቅት የተገኙት የፌደራል በጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበራት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ፈንታዬ ገዛኸኝ "  ድርጅቶችን በመደገፍና በመከታተል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የመንግስት መዋቅር ሚና ነው " ብለዋል። በኢትዮጵያ 3ሺህ  400 በጎ አድራጎት ደርጅቶችና ማህበራት እንዳሉ ጠቁመው እነዚህም  መንግስት ያልደረሳባቸው አካባቢዎች በመሸፈን የጀመሩትን የልማት ስራ ግልጽነት ባለው አካሄድ ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም