በአሸባሪው ሃይል እየተካሄደ ያለው ወረራ፣ ጥቃት፣ ዘረፋና ግድያ ሁሉም በአንድነት ሊመክተው እና የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ኢትዮጵያን መታደግ ይገባል--አቶ ደመቀ መኮንን

100

ነሀሴ 2/2013 (ኢዜአ) በአሁን ሰዓት በአፋር እና በአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች በአሸባሪው ሃይል እየተካሄደ ያለው ወረራ፣ ጥቃት፣ ዘረፋና ግድያ ሁሉም በአንድነት ሊመክተው እና የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ኢትዮጵያን መታደግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የፌዴራል እና የክልል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቡድን እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ በጋይንት ጨጨኾ አቅጣጫ በመቄት ወረዳ ደብረ~ዘቢጥ አካባቢ የመስክ ጉብኝት አካሄዷል።

በጋይንት ጨጨኾ አቅጣጫ በመቄት ወረዳ ደብረ~ዘቢጥ አካባቢ ወረራ፣ ጥቃት፣ ዘረፋና ግድያ እያካሄደ ያለውን የአሸባሪ ሃይል ለመመከት የተሰለፈውን የመከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ አደረጃጀት እንቅስቃሴ ቡድኑ በጉብኝቱ ተመልክቷል።

የአሸባሪውን ሃይል እኩይ እንቅስቃሴ እና ድርጊት ለመመከት ከጋይንት ጀምሮ የአከባቢው ማህበረሰብ በከፍተኛ ወኔ እና ቁርጠኝነት የሚያደርገውን ጠንካራ ዝግጅት ቡድኑ ለመታዘብ ችሏል።

በየአከባቢው የሚገኘው ማህበረሰብ ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከልዩ ሃይሉ፣ ከሚሊሻ እና ከፋኖ ጋር በመቀናጀት ሃገርን የመታደግ ታሪካዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ዝግጅት የሚያስደንቅ መሆኑን አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

የአከባቢው ማህበረሰብ ለሰራዊቱ፣ ለልዩ ሃይሉ፣ ለሚሊሻው እና ለፋኖ አደረጃጀት ጠንካራ ደጀንነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን በጉብኝቱ መታዘብ መቻላቸውን ገልፀዋል።

በመጨረሻም በአሁን ሰዓት በአፋር እና በአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች በአሸባሪው ሃይል እየተካሄደ ያለው ወረራ፣ ጥቃት፣ ዘረፋና ግድያ ሁሉም በአንድነት ሊመክተው እና የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ኢትዮጵያን መታደግ እንደሚገባ አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም