አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአሸባሪው ህወሃትን ወረራ ከጸጥታ ሃይሎች ጎን በመሆን ሁሉም ሊመክተው እንደሚገባ አስገነዘቡ

69

ባህር ዳር፣ ነሐሴ 02 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት እያካሄደ ያለውን ግልጽ ወረራ ለመቀልበስ ወጣቱ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ሊፋለመው እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ።

በባህር ዳር ከተማ የህልውና ዘመቻ የክተት ጥሪን ተቀብለው ወደ ስልጠና የገቡ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኝ ተጠባባቂ ሃይሎች ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ አቶ ገዱ ባስተላለፉት መልዕክት "አሸባሪው ህወሓት እያካሄደ ያለው ጦርነት አገሪቱን ለውድቀት ለመዳረግና የህዝብን ክብር ዝቅ ለማደረግ ያለመ ነው" ብለዋል።

ስለሆነም ጦርነቱን ለመመከት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አገሪቱን ለውድቀት ለመዳረግና የህዝብን ክብር ዝቅ ለማድረግ በግፍ የተከፈተ ጦርነትን መመከት የሚቻለው ፊት ለፊት በመጋፈጥ ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።

"ወጣቶችም በቁርጠኝነት ተሰልፋችሁ የክልላችሁን ህዝብ እያጎሳቆለ ያለውን የሽብር ቡድን ለመመከት ቁርጠኛ ሆናችሁ መሰለፍ አለባችሁ" ሲሉም አሳስበዋል።

የጥፋት ሃይሉ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ህብረተሰቡ ለዘመናት ያፈራውን ንብረት እያወደመና እየዘረፈ መሆኑን ገልጸዋል።

"ይህንን ወረራ መመከትና ለእውነት የሚከፈል መስዋዕትነት የህዝባችንን ክብር ከፍ ለማድረግ፤ የሀገራችንና የህዝባችንን ህልውናም ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ ነው" ብለዋል።  

''ወረራውን ለመመከት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሃላፊነት አለበት'' ያሉት ደግሞ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ናቸው።

"የደፈረንን ሃይል በመጣበት አግባብ መደምሰስ አለብን፤ መቀበርም አለበት" ያሉት አቶ ላቀ፤ የአባቶችን ታሪክ በመድገም የክልሉን ክብር መመለስ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ታሪክ እንዳይበላሽም አሸባሪውን ህወሃት መመከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የወጣቱ ተነሳሽነትና ቁጭት መልካም እንደሆነ ጠቁመው፣ "በዚህ ሰዓት በግንባር በመሰለፍ ክልሉንና አገሪቱን ነጻ ለማውጣት መቁረጥ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ምሩቅ ተጠባባቂ ሃይሎች ከመከላከያ፣ ልዩ ሃይሉ እና ሚሊሻዎች ጋር ተሰልፈው መፋለምን ጨምሮ የአካባቢን ሰላም የማስጠበቅና ሰርጎ ገቦችን አድኖ የመያዝ ሃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።

"ከእዚህ በኋላ ይህ ወጣት እያለ የአማራ ህዝብ አንገቱን አይደፋም" ያሉት ዶክተር ድረስ፣ ህዝቡ ወደ ነበረበት ከፍታ እንደሚመለስ አረጋግጠዋል።

የአገርን ክብር ሊያዋርድና ታሪክን ሊበትን የመጣን አሸባሪ ቡድን ፊት ለፊት በመግጠም ለመመከት መዘጋጀታቸውን ተመራቂ ተጠባባቂ ሀይል አባላቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም