እኛ እያለን የአሸባሪው ህወሃት አገር የማፍረስ ሴራ አይሳካም…የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች

132

አርባ ምንጭ  ሐምሌ 30/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት አገር የማፍረስ ሴራ እንዳይሳካ ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት በደጀንነትና በስንቅ ዝግጅት እየገለጹ ከሚገኙት የአርባምንጭ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ስንታየሁ አበረ አንዷ ናቸው።

አሸባሪው ህወሃት የአገራችንን ልማት ከማደናቀፍም በላይ ትውልድ ለማጥፋት ህፃናትን ወደ ጦር ግንባር እየማገደ ይገኛል” ነው ያሉት።

ከእኔ ውጭ ሌላው አገር መምራት የለበትም በሚል አስተሳሰብ የመንግስትንና የህዝብን አቅም ለማዳከም ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ከፈጸመው ጥቃት ይባስ ብሎ በማይካድራ ንጹሃን ህዝብ ላይ ያደረገው ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ታሪክ የማይረሳው ጠባሳ እንደሆነ አስረድተዋል።

የአገራችን ሉዐላዊነት ለማስከበር ከተሰለፉ ወገኖቻችን ጎን መሆናችን ለመግለጽ በጋራ ስንቅ እያዘጋጀን ነው ብለዋል።

ከአገር በላይ ሌላ ምንም ነገር የለም ያሉት ሌላኛዋ ወይዘሮ ካዎቴ ኤቃ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃትን በግንባር ተገኝቶ እንዲፋለም ከስድስት ወራት በፊት ልጃቸውን መሸኘታቸውን ተናግረዋል።

“የመከላከያ ሠራዊታችን የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት የሚችለው እኛ ከጎኑ መሆናችን ስናሳይ ነው” ብለዋል።

“የአገር ጉዳይ የሁሉም ዜጋ ጉዳይ በመሆኑ ከጥንት ጀምሮ የነበረንን አንድነት የበለጥ የምናጠናክርበት ጊዜ ነዉ” ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ገነት ደመረ በበኩላቸው “ፋሺስት ጣሊያንን መገርሰስ የቻልነዉ ለአገራችን ህልዉና ለመዋደቅ ሁላችንም አንድ መሆናችን ነዉ” ብለዋል።

“በዚያ ጦርነት ትግሉን ከመምራት ጀምሮ የስንቅ ዝግጅትና የሞራል ድጋፍ በማድረግ የሴቶች ድርሻ ጉልህ ነበር” ብለዋል።

በአሸባሪዉ ህወሃት የተቃጣብን ጦርነት በጋራ ለመመከት የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶች ከራሳቸዉ መቀነት 18 ኩንታል የሚሆን በሶ፣ዳቦቆሎና ኩኪስ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡

ሉዓላዊነቷን በማስጠበቅ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነችዉን ታሪካዊ አገርን ለማዳከም ከአሸባሪው ህወሃት ጎን በመሆን ምዕራባዊያን እያሳደሩብን ያለዉን ጫና ለመቋቋም የአፍሪካ ህብረት ድምጹን እንዲያሰማ ጠይቀዋል፡፡

መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት ሲል የወሰነውን የተኩስ አቁም እርምጃ ተገቢ ቢሆንም አሸባሪዉ ይህንን ወደ ጎን በመተዉ የዜጋዉን ደም የማፋሰስ ተግባሩን ተያይዞታል ነዉ ያሉት፡፡

ሴቶችን አስገድዶ በመድፈርና ህፃናትን ለጦርነት በመማገድ አስከፊ ተግባር በትግራይ ልጆች ላይ እየፈጸመ በመሆኑ ዓለም ሊያውግዘው እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ህዝብ ሰሞኑን 2ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊት በማድረግ አለኝታነቱን አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም