አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የአገር ሉዓላዊነትና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ላይ ሊያተኩር ይገባል- ፖለቲከኞች

112

አዲስ አበባ፣  ነሃሴ 01/2013(ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የአገር ሉዓላዊነትና የህዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ ላይ ማተኮር እንዳለበት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለራሱ እንዲያመቸው ባጸደቀው ህገ- መንግስቱ ታግዞ የዘራው የጥላቻና አብሮ የመኖር እሴት መሸርሸር አገሪቷን ለከፋ ጉዳት እየዳረጋት ይገኛል።

የህዝብ አብሮነትና አንድነትን ለመመለስና የአገር ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠውን ችግር እስከ ወዲያኛው ለመቀልበስ በህዝብ የተመረጠው መንግስት አበክሮ መስራት እንዳለበት ፖለቲከኞቹ ይናገራሉ።

የኢዜማ ፓርቲ  ከፍተኛ አመራር አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ለረጅም ዓመታት በአሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተዘራው የክፋትና የግለኝነት ስራ የህዝብ ደህንነትና የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ ጥሏል።

በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ዜጎች በማንነታቸው ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ፣ እየተገደሉና የያዙትን ሃብትና ንብረት እየተቀሙ ይገኛሉ።

አሁንም አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያን አንድነት ከማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች በር በመክፈት በአገሪቷ ውስጥ ትርምስ ለመፍጠር ከባንዳዎች ጋር እየሰራ ይገኛል።

በመሆኑም በህዝብ ተመርጦ ወደ ስልጣን የሚመጣው አዲስ መንግስት የአገር ሉዓላዊነትንና የህዝብ አንድነትን በተጠናከረ መልኩ ለማስጠበቅ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል አቶ ግርማ።

ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪው ትውልድ የሚሆኑ መልካም እሴቶችን በጽኑ መሰረት ላይ አኑሮ ማለፍ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባዋልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የገባችበትን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግር ለመፍታት የተቋማት አደረጃጀቶች ላይ ማተኮር እንዳለበትም ጠቁመዋል።


በጥቃቅን ስራዎች ላይ በማተኮር የአገር አንድነትን የሚያፈርሱ ተቀዳሚ ስራዎች እንዳይረሱ በማድርግ ለህዝብ አንድነት እንቅፋት የሆኑ የህገ - መንግስት ክፍሎችን ማሻሻል ያስፈልጋል ነው ያሉት አቶ ግርማ ሰይፉ።

‘’ህገ መንግስት በወርቅ የተጻፈ ጽላት አድርጎ የማሰብ ጊዜ ማብቃት አለበት፣ ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ መሻሻል አለበት" ብለዋል።

የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌው፤ በቀጣይ የሚመሰረተው መንግስት በአገር አንድነት ላይ አበክሮ መስራት አለበት ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓትና ግብረ አበሮቹ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የአገሪቷን ህዝብ ለመከፋፈል በሰሩት ስራ ዛሬ ለህዝብ ሰላም ማጣትና ለአገር አንድነት ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ነው የገለጹት።

የአሸባሪውን ህወሓት ከፋፋይ አጀንዳ በመዝጋት የህዝቡን አንድነት በሚያስጠብቁ ስራዎች ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።

የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያ ለማፍረስ የሚደረገውን ጥረት በህዝብና መንግስት ጠንካራ ትብብር ማስቆም ይገባል ሲሉ ፖለቲከኞቹ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም