ወሰን ተሻጋር ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎታቸውን በአዳማ ጀመሩ

60
አዳማ ነሀሴ 3/2010 ወጣቶች ወሰን ሳይገድባቸው በልማትና ገፅታ ግንባታ መሳተፋቸው  ሀገሪቷ ለጀመረችው የለውጥ ጉዞ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ገለጹ። ወሰን ተሻጋር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች በኦሮሚያ ደረጃ ዛሬ በአዳማ ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸው በይፋ ሥራ ጀምረዋል። የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ እንደገለጹት ወጣቶች ወሰን ሳይገድባቸው በልማትና የገፅታ ግንባታ ላይ መሳተፋቸው  ሀገሪቷ ለጀመረችው የለውጥ ጉዞ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ያለንበት ወቅት የፍቅር፣ ይቅርታ፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና የመደመር በመሆኑ ወጣቶች ወሰን ሳይገድባቸው በማህበራዊ ልማትና በሌሎች መሳተፋቸው ጥሩ ልምድ የሚያገኙበትና የህዝቦችን ባህልና ታሪክ የሚያውቁበት ፕሮግራም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች ይዘው የመጡትን ተልዕኮና ዓላማ ከዳር እንዲያደርሱ መስተዳደሩ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ''ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይዘው የተነሱትን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ከዳር ማድረስ የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሀገራዊ አንድነትና የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት ውስጥ የድርሻውን መወጣት ሲችል ነው'' ብለዋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች በአዳማና አካባቢዋ የሚያከናውኑት የዕለት ተዕለት ሥራቸው ታሪክ የማይረሳው መሆን እንደሚገባም ከንቲባው አስገዝበዋል። የኦሮሚያና ኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር በበኩሉ ወጣቶች ከትውልድ አካባቢያቸው ውጪ በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች የበጎ ሥነ ምግባር ተግባር ማከናወን የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክር ከመሆኑም ባሻገር በሀገር አንድነት ግንባታ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጿል፡፡ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባህል፣ ታሪክና ቋንቋን ጭምር የሚማሩበትና ልምድ የሚለዋወጡበት መሆኑን አስረድተዋል። ወጣቶቹ በከተማዋና አካባቢዋ የ10 ቀናት ቆይታቸው በጽዳትና ውበት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ፣ ደም ልገሳ፣ የጎልማሶችና የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአረጋዊያን እንክብካቤና ድጋፍ ተግባር እንደሚያከናውኑ የአዳማ ከተማ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት እሱባለው ግርማ ተናግረዋል። በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ አዳማ ከመጡት መካከል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ተወላጅ ወጣት አህመድ ሲራጅ እንደገለጸው ከክልሉ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገሪቷን ህዝቦች በማህበራዊና ሰብዓዊ ድጋፍ ለማጋዝ መምጣቱን ተናግረዋል። በቆይታውም ከህብረተሰቡ ጥሩ ልምድና ተሞክሮ እንደሚያገኝ ጠቅሶ በዚህም የህዝቦች ትስስርና የሀገር አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል። ወስን ተሻገር የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መጀመሩ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ውስጥ ሚናው የጎላ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ከደቡብ ክልል የመጣው ወጣት ፀጋዬ ተሰማ ነው። ''እኛ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች የሀገራችን  ፍትህ፣ ዴሞክራሲና አንድነት ማረጋገጥ በሚቻልበት ብሎም ልማትና እድገቷን ማፋጠን ላይ መስራት የምንችለው ብዙ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እዳ አለብን'' ብለዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ሥራ በየደረጃው የሚገኙ ወጣቶችን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም