አሜሪካ ለጤና ዘርፍ የሚውል ተጨማሪ ድጋፍ አድርጋለች – ሳማንታ ፓወር

819

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29/2013 (ኢዜአ) አሜሪካ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና ለአስቸኳይ እርዳታ ድጋፍ የሚውል ከ45 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጓን የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩ ኤስ ኤድ/ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የዩ.ኤስ.ኤድ ኃላፊዋ ሳማንታ ፓወር ትናንት ምሽት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች ድጋፍ በማድረግ ጠንካራ አጋር ነው ብለዋል።

ለአብነትም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አሁንም የጤና ሥርዓቱን ለመደገፍ በተለይም ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚደረገውን ብሔራዊ ጥረት ለመደገፍ የሚውል ከ45 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም ድጋፉ በዘርፉ ለሚካሄደው አስቸኳይ የሠብዓዊ እርዳታ እንደሚውል ነው የጠቆሙት።  

ድጋፉ የአሜሪካ መንግሥት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት ኮቪድ-19ን ለመከላከል አዲስ የመደበው 445 ሚሊዮን ዶላር አካል መሆኑን ገልጸዋል።

የገንዘብ ድጋፉ የአፍሪካ ኅብረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ከመከላከያ ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ መሆኑንም ሃላፊዋ አንስተዋል።

በተጓዳኝም ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ  በርካታ እመርታዎች ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

በተለይም ወባና ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል እንዲሁም በእናቶችና ሕጻናት ጤና ላይ በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በትግራይና በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ለችግር ለተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚውል የእህል ክምችት በድርጅታቸው መኖሩንም ጠቁመዋል።

በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍም “በዩ.ኤስ.ኤድ የእህል መጋዘን 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ ክምችት አለ” በማለት ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች አገር መሆኗን ገልጸው የአገራቱ ግንኙነት ከድጋፍ ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ሊያድግ እንደሚገባው ገልጸዋል።