የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ሠራዊቱ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ አቅም ይሆነዋል

69

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሀምሌ 29/2013  የኢትዮጵያ ሕዝብ እያደረገው ያለው ድጋፍ የመከላከያ ሠራዊቱ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ አቅም እንደሚሆነው የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጅ ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ የደቡብ ክልል ሕዝብና መንግስት ለሠራዊቱ ያደረገውን ድጋፍ በምድር ሃይል ቅጥር ግቢ ተረክበዋል።

ክልሉ ለሁለተኛ ዙር በዓይነትና በገንዘብ ያሰባሰበውን ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እያደረገው ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ ስንቅ፣ ወኔና ሞራል ይሆነዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የደቡብ ክልል ሕዝብና መንግስት ላበረከቱት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡፡ 

ለአገሩ ሉዓላዊነት መከበር መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘወ ሠራዊት የሕዝቡ ድጋፍ ይበልጡን የሚያበረታታው መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት የጀመረውን የአገር ሕልውና የማስጠበቅ ዘመቻ በድል ያጠናቅቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሕዝቡም አሁን ባለው ሞራል ከመንግስት ጎን እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ድጋፉን ያስረከቡት የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አባተ ተፈሪ ክልሉ ለሁለተኛ ዙር ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከዚሁ ድጋፉ ውስጥ ከ40 ሚሊዮን 243 ሺህ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን 26 ሚሊዮን 697 ሺህ በላይ የሚሆነው በዓይነት መቅረቡን አስረድተዋል፡፡ 

በአጠቃላይ ክልሉ በሁለት ዙሮች ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንና ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በበኩላቸው ከክልሉ በርካታ ወጣቶች ሠራዊቱን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁንም በራሳቸው ፈቃድ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል የወሰኑ ወጣቶችን ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም