ዶክተር ጌታሁን ጋረደው የወላይታ ዞን ዋና አስተዳደሪ ሆነው ተመረጡ

101
ሶዶ ነሀሴ 3/2010 የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አራተኛ ዙር ስድስተኛ ዓመት  አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ዶክተር ጌታሁን ጋረደውን የዞኑ  ዋና አስተዳደሪ አድርጎ መረጠ፡፡ በሶዶ ከተማ በተካሄደው ጉባኤ ምክር ቤቱ ዋና አስተዳደሪውን የመረጠው  በዞኑ ደኢህዴን አቅራቢነት ነው፡፡ የዞኑ ደኢህዴን ቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዋዱ ዳና በዚህ ወቅት እንደገለጹት ከዚህ በፊት ዞኑን ሲመሩ የነበሩት አቶ አስራት ጤራ ወደ ክልል በመሄዳቸው ምክንያት አዲስ አስተዳደሪ መመረጥ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ዶክተር ጌታሁን ጋረደው የተተኩት። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን የለውጥ ንቅናቄ በተገቢው ለማስቀጠል በልምድ፣ በትምህርት አግባብነትና ባላቸው የስራ ተነሳሽነት የዞኑ ዋና አስተዳደሪ ሆነው ተመርጠዋል። ዶክተር ጌታሁን ከዚህ ቀደም የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳደሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ተመራጩ ዋና አስተዳደሪ  በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ስልጣኑን ተረክበዋል፤ የተጓደሉ አምስት የተለያዩ መምሪያ ኃላፊዎች አቅርበው በሙሉ ድምፅ አፀድቀዋል። በዚህም  አቶ ዳጋቶ ኩምቤ የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳደሪና የፍትህ መምሪያ እና አቶ አክሊሉ መኮንን የዞኑ ፀጥታና አስተዳደር ኃላፊዎች ሆነዋል። አቶ ሚካኤል ሳኦል የዞኑ ትምህርት መምሪያ ፣ አቶ አለማየሁ  ጎልዳ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ፣ አቶ ዘካሪያስ ወልታሞ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ መምሪያ ኃላፊዎች  ሆነው ተሹመዋል።   አምስቱ ተሿሚዎች ከወጡ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የተተኩ ሲሆን ቀደም ሲልም በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ላይ ሲሰሩ የቆዩ ናቸው የምክር  ቤቱ ጉባኤ በተጨማሪም ለ2011 የስራ ዘመን ከ2 ቢሊዮን 900ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም