መገናኛ ብዙሃን በሁለተኛው ዙር ምርጫ ለህዝብ መረጃዎችን በማድረስ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

96

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሀምሌ 28/2013 ኢትዮጵያ ጳጉሜን 1 ለምታካሂደው ሁለተኛው ዙር ምርጫ መገናኛ ብዙሃን በሁለተኛው ዙር ምርጫ ለህዝብ ትክክለኛ መረጃዎችን በማድረስ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ሚዲያ ድጋፍ ከአለም አቀፍ ሚዲያ ድጋፍ ጋር በመተባበር መገናኛ ብዙሃን በ6ኛ አጠቃላይ ምርጫ የነበራቸው ተሳትፎና በቀጣይ መስራት ያለባቸው ጉዳይ ላይ መክሯል።

በመድረኩ ከምርጫ ጋር በተገናኘ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አብዲሳ ዘርአይ የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል።

በጥናታቸውም መገናኛ ብዙሃን በ6ኛው አጠቃላይ የምርጫ ሂደት በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ የነበራቸው አጠቃላይ ተሳትፎ መልካም መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በተወሰኑ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ምርጫው በሁለት ዙር እንዲካሄድ መወሰኑን ተከትሎ በመጀመሪያው ዙር መረጃን ለህዝብ በማድረስ በኩል የተሻለ ስራ መስራታቸውን ጨምረዋል።

በቅድመ ምርጫ በመራጮት ትምህርትና ሌሎች መረጃዎችን ለመራጩ ህዝብ በማቅረብ፣ በድምጽ መስጫ እለትም የነበሩ ሁነቶችን በቀጥታ ማሰራጨታቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በቀጣይ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች  ጳጉሜን 1 የሚደረግ በመሆኑ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክረዋል።

ቀደም ሲል ሲያደርጉ እንደነበረው ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ፣ የምርጫ ቦርድ ዝግጅት፣ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችንና ሌሎች መረጃዎችን ለመራጩ ህዝብ ማድረስ እዳለባቸው ጨምረዋል።

የሚዲያ ተንታኙ አቶ ገመቹ በቀለ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በምርጫ ዕለት የነበራቸውን ተሳትፎና የተወሰዱ ልምዶችን በተነተኑበት ጹህፋቸው በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የነበሩ አወንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎችን ዘርዝረዋል።

ኢትዮጵያ ካለባት ውጫዊና ውስጣዊ ጫና አንጻር ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ መገናኛ ብዙሃን የነበራቸው አስተዋጽኦ ጉልህ እንደነበር ተናግረዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ በኩል የቦርዱን ተአማኒነት ለማሳጣት የነበሩ ዘመቻዎች፣ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ በአገር ውስጥ ያለው አለመጋጋት የምርጫው ተአማኒነት ላይ ጫና እንዳለው አድርገው ማቅረብ የነበሩ አሉታዊ ጎኖች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በድህረ ምርጫ፤ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁንና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚሰጣቸው መረጃዎች ውጪ በሚወጡ መረጃዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ መረጃዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር አውስተው ጳጉሜን 1 ለሚደረገውም በተመሳሳይ ሃላፊነታቸውን እንዲመጡ ጠይቀዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚዲያ ተሳትፎ አማካሪ አቶ ዮሴፍ መርጉ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰራቸው ተግባራት እንዳሉ ሆነው መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነት በተሞላው መንገድ መዘገባቸው ለምርጫው ሰላማዊነት  ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

በቀጣይ  ጳጉሜን 1 ለሚደረገው ምርጫ እስካሁን ሲያደርጉ እንደነበረው የምርጫ አዋጅና መመሪያዎችን ተከትለው እንዲሰሩ እናበረታታለን ብለዋለ።

ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም