መዲናችን የመጽሐፍት ካፌዎች ያስፈልጓታል

98
አዲስ አበባ ነሀሴ 3/2010 በአዲስ አበባ በርካታ የመጽሀፍ ካፌዎች እንደሚያስፈልጓት ተገለጸ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ያለው ጃዝ ኮፊ  ከሌሎች ካፌዎች በተለየ መልኩ በመጽሐፍት የተሞሉ መደርደሪያዎችን ተመለከትን። በመዲናዋ ካሉ ካፌዎች የተለየ በመሆኑ ትኩረታችንን ስለሳበው ባለቤቱን ለማነጋገር ወደድን። ብዙዎቹ የመዲናዋ ካፌዎች ተስተናጋጅ በካፌዎቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ካገኘ በኋላ ወንበር እንዲለቅላቸው የሚፈልጉ ሆነው ሳለ ይህ 'የአንባቢ ያለህ' በሚል መጽሐፍት ደርድሮ ደንበኛውን የሚጠብቅ ካፌ ሊበረታታ ይገባል። የካፌው ባለቤት ወጣት ዳዊት አዲስ ይባላል። ተወልዶ ያደገው አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ገዳም ሰፈር ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው። አብዱ ኪያር እንዳቀነቀነው "የአብሮ መብላት ተሳስቦ ኑሮ ገዳም ሰፈር ቀረ ድሮ" የሚለው ስንኝ ድሮ ብቻ ሳይሆን አሁንም መተሳሰብ በዚያ ሰፈር መኖሩን ለማሳየት የተከፈተ ካፌ ነው። በካፌው ውስጥ ባሉ መደርደሪያዎች በርካታ የተለያዩ መጽሐፍት ተደርድረዋል። ካፌውን የንባብ ቤት በማድረግ ወጣቱ የንባብ ባህሉን እንዲያዳብር እንዲሁም የተሻለ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ ለመፍጠር በማሰብ የተከፈተ መሆኑን ነው ወጣት ዳዊት ለኢዜአ ሪፖርተር የተናገረው። "አንድ ቤት መጽሐፍ የለውም ማለት ነብስ እንደሌለው ስጋ ነው የምቆጥረው" ያለው ወጣት ዳዊት በትምህርት ካገኘው እውቀት ባሻገር ከመጽሐፍት ያገኘው እውቀት ህይወቱን እንደቀየረው ይናገራል። ለአንድ ሰው ጤንነቱን ለመጠበቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚያደርገው ሁሉ ሰዎች የተሻለ አስተሳሰብ እንዲኖራቸውና በነገሮች ላይ ያላቸውን ምልከታ ሚዛናዊ ለማድረግ አእምሮን በንባብ ማሳደግ ያስፈልጋል ይላል ወጣት ዳዊት። የካፌው ዋና ተግባር የንባብ ባህልን ከማሳደግ ባሻገር በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ግንኙነት በመፍጠር የሀሳብ ልውውጥ ለማዳበር እንደሆነም ወጣት ዳዊት አጫውቶናል። በአዲስ አበባ ብዙ ሲዘወተር ያላየነው የመጽሐፍት ካፌ በወጣት ዳዊት ተነሳሽነት መከፈቱ እንዳስደሰታቸው የካፌው ተገልጋይ ወጣቶች ይገልጻሉ። በተለይ ወጣቶች በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን ከሚያባክኑ ይልቅ በዚህ የመጽሐፍት ካፌ ቢውሉ የንባብ ልምድን በማዳበር እውቀታቸውን ከፍ ማድረግ ይችላሉ ብለዋል። ወደ ካፌው ስትመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጸችው ወጣት አማረች እሜ ካፌው የንባብ አገልግሎት መስጠቱ ወጣቱ ከአልባሌ ቦታዎች ራሱን እንዲቆጥብ ያደርጋል ብላለች። አብርሃም ፋንቱ የተባለው የካፌው ተጠቃሚ በበኩሉ "ለሌሎች ካፌዎች የማስተላልፈው ከሚሸጡት ሻይ ቡና ባለፈ ይህን ስራ ጎን ለጎን ቢያስኬዱት ከማርኬቲንግ አንፃር አሪፍ ገቢም ያገኛሉ ከምግብና መጠጥ ሽያጭ በተረፈ እውቀትንም ይሸጣሉ ማለት ነው" ብሏል በካፌው ተጠቃሚዎችና በባለቤቱ ወጣት ዳዊት  በቀጣይ የንባብ ባህልን ለማዳበር በካፌው ውስጥ በመጽሐፍቶች ላይ የውይይት መድረክ እንደሚኖር ጠቁሞ ህብረተሰቡ ምንም ነገር መጠቀም ሳያስፈልገው መጽሐፍ አንብቦ መሄድ ይችላል ብሏል ወጣት ዳዊት። ምንም ሳይጠቀሙ መቀመጥ ክልክል ነው የሚል ማስታወቂያ በሚለጠፍባቸው የአዲስ አበባ በርካታ ካፌዎች እንዲህ ዓይነት በጎ ተግባር ማየታችን ይበል የሚያሰኝ በጎ ተግባር ነው። ሌሎች ካፌዎችም ይህን ተግባር በማስፋት አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል ባይ ነን።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም