በትግራይ ክልል በ12 ወረዳዎች የተከሰተውን የአተት በሽታ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

97
መቀሌ ነሀሴ 3/2010 በትግራይ ክልል በ12 ወረዳዎች የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡ የክረምት ዝናብን ተከትሎ በሚከሰተው ጎርፍ የውሃ ምንጮች ለብክለት እየተዳረጉ በመሆኑ ህብረተሰቡ ውሃ አፍልቶ እንዲጠቀም ቢሮው አሳስቧል፡፡ በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ገብረዋርያ ለኢዜአ እንደገለጹት በሽታው ዳግም ያገረሸው በግልና በአካባቢ ንጽህና ጉድለት ነው፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ የግልና የጋራ የመጸዳጃ ቤቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖርና የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለበሽታው መስፋፋት ምክንያቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የመስተዳድር አካላት ለዘርፉ የሚሰጡት ትኩረት አነስተኛ መሆንም በሽታው እንዲስፋፋ ሌላው ምክንያት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ እስካሁን በበሽታው ምክንያት የሞተ ሰው አለመኖሩን የገለጹት አቶ ዮሐንስ በበሽታው የተያዙ 114 ሰዎች ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡ በመቀሌ የአተት በሽታ በተደጋጋሚ ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ ሓድነት ክፍለ ከተማ ነው፡፡ በክፍለ ከተማው ከ26 መኖሪያ ቤቶች በአማካይ ስድስቱ ብቻ የግል መጸዳጃ ቤት እንዳላቸው የጤና ባለሙያዎች ባደረጉት ጥናት መረጋገጡንና ይህም ለችግሩ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቀሪው ማህበረሰብ ከመጸዳጃ ቤት ውጭ ስለሚጸዳዳ ለአተት በሽታ ለመከሰት ዋና ምክንያት እንደሆነ መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡ የሓድነት ክፍለ ከተማ ጽዳትና ውበት አስተባባሪ አቶ ክፍለማሪያም ብርሃነ ስለጉዳዩ ተጠይቀው እንዳሉት በክፍለከተማው ለጸበል ወደእምነት ተቋማት የሚመጡ በርካታ ሰዎች መኖራቸውና ተገቢ ጥንቃቄ አለመደረጉ በሽታው በተደጋጋሚ እንዲከሰት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡  በአሁኑ ወቅት በእምነት ቦታ ጸበሉ መበከሉ በመረጋገጡ ህብረተሰቡ ለመጠጥ እንዳይጠቀሙበት ትምህርት በመሰጠት ላይ መሆኑን አመልክተዋል። የግል መፀዳጃ ቤት የሌላቸው ነዋሪዎች ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶች እንዲሰሩ እየተደረገ ነው ብለዋል። በነባር ይዞታ ስር ያሉ ነዋሪዎችም የከተማው ፕላን እስኪጸድቅላቸው ድረስ ጊዜያዊ መፀዳጃ ቤቶች ገንብተው እንዲጠቀሙ  ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡ የግልና የአካባቢ ንፅህናን ለማስጠበቅም መኖሪያ ቤቶችን በመፈተሽና በመከታተል የተሻለ ሥራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። ከመኖሪያ ቤት የሚወጡ ደረቅ ቆሻሻዎች በየቀኑ እንዲነሱ የክፍያና የአደረጃጀት ለውጥ በመደረግ ላይ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ልማትና የከተማ ውበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዳነ ገብረፃዲቅ ናቸው፡፡ የከተማውን ጽዳትና ውበት ለመጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ ህብረተሰቡ በአካባቢ ጽዳትና ውበት እንዲሁም ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሻሽል አሳስበዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም