ዳጉሳን በችግኝ መልክ ማልማት የተሻለ ውጤት እያስገኘላቸው መሆኑን በፀለምት ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

125
ሽረ እንዳስላሰ ነሀሴ 2/2010 የዳጉሳ ሰብል በችግኝ መልክ አዘጋጅተው በማልማት ከተለምዶው አሰራር የተሻለ ውጤት እያስገኘላቸው መሆኑን በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ፀለምት ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ የዳጉስ ሰብል ክረምት ከመግባቱ በፊት በችግኝ መልክ አዘጋጅቶ በመቆየትና ክረምት ሲገባ የመትከሉ  ስራ በሙከራ ደረጃ በአካባቢው ላለፉት አምስት  ዓመታት  ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በፀለምት ወረዳ በተያዘው የመኽር ወቅት 150 ሄክታር መሬት ዳጉሳ በችግኝ መልክ  ተተክሎ እየለማ ነው፡፡ አርሶ አደር ጥጋቤ ትኩእ በወረዳው ሰቆጣ ስላሴ ቀበሌ አሰራሩን ተግባራዊ ካደረጉ ገበሬዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት " ዳጉሳን አፍልቶ በችግኝ  መልክ በመትከልና ማልማት በህይወት ዘመኔ  ከለመድኩት የእርሻ ስራ ጋር የበለጠ በሄክታር ከሶስት እጥፍ በላይ   ምርት እንዳገኝ አስችሎኛል" ብለዋል፡፡ በዘልማዳዊ የብተና አዘራር ከአንድ ሄክታር መሬት ያገኙት የነበረው  የዳጉሳ ምርት ከ11 ኩንታል እንደማይበልጥ ጠቁመው በበጋ ወቅት በአነስተኛ መሬት የዳጉሳ ችግኝ አዘጋጅተው ክረምት ሲገባ እየተኩሉ በማልማት በሄክታር እስከ 40 ኩንታል እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ " ምንም እንኳን በችግኝ መልክ ዳጉሳን ማልማት አድካሚና ጉልበት የሚጠይቅ ቢሆንም ውጤቱ ግን አርኪ ነው "ያሉት ደግሞ የዚሁ  ቀበሌ ገበሬ አርሶ አደር በላይ እጅጉ ናቸው። ባለፈው የምርት ወቅት ዳጉሳን በችግኝ መልክ አዘጋጅተው  በመትከል ካለሙት ግማሽ ሄክታር ማሳቸው 18 ኩንታል ምርት መግኘታቸውን ጠቅሰው ይህም ከተለመደው አስራር የተሻለ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተያዘው የመኽር ወቅትም የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችንና ግብአትን በአግባቡ በመጠቀም  ግማሽ ሄክታር መሬት ዳጉሳ በችግኝ መልክ አልምተዋል፡፡ በወረዳው ሴት አርሶ አደር እምባፍረሱ ተጨና በበኩላቸው ዳጉሳን በችግኝ መልክ ማልማት  ሰብሉ ከአረም ነፃ ከማድረግ በተጨማሪ ከፀረ ሰብል ተባዮች ለመከላከልና በቀላሉ ለመሰብሰብ አመቺ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳጉሳን በችግኝ  መልክ ተክሎ ማልማት የተጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት እንደሆነ የወረዳው የግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ መኮንን አመልክተዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት በግማሽ ሄክታር ማሳና በሁለት አርሶ አደረች የተመጀመረው የዳጉሳ ተክል ልማት አሁን እየሰፋ መጥቶ የተጠቃሚ  አርሶ አደሮችም  ቁጥር ወደ 158 ከፍ ብሏል፡፡ በተያዘው የመኽር ወቅትም በወረዳው 150 ሄክታር ማሳ ዳጉሳን  በችግኝ  መልክ ተተክሎ እየለማ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰብሉ ተጠቃሚ  የሆኑ አርሶ አደሮች 300 ያህል ደርሰዋል፡፡ የዳጉሳ ሰብል ምርት ለመስጠት ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ክረምት ሲገባ በብተና መዝራት ለዝናብ እጥረት የመጋለጥ እድሉ ሰፊ መሆኑን አቶ በላይነህ  ተናግረዋል፡፡ " ጊዜው በችግኝ ማፍያ ቦታ ላይ ሲቆይ እድገቱ ጨምሮ በመምጣት ማሳ  ላይ ሲተከል በቂ ዝናብ ስለሚያገኝ የተሻለ ምርት እንዲሰጥ ያደርገዋል" ብለዋል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም